Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የነቢዩ ሙሐመድ የልደት በዓልን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የነቢዩ ሙሐመድ (ሠዓወ) የልደት በዓልን አስመልክቶ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ።

እንኳን ለ1494ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል ‹መውሊድ አን’ነቢ› አደረሳችሁ፡፡

በእስልምና የዘመን አቆጣጠር ራቢአል አወል የተሰኘው ሦስተኛው ወር በገባ በ12ኛው ቀን በየዓመቱ የሚከበረው ‹‹መውሊድ›› የቃል ምንጩ ዐረብኛ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹የመወለጃ ቦታ ወይም የመወለጃ ዕለት›› ማለት ነው፡፡ መውሊድ በመንፈሳዊ ትርጉሙ ደግሞ ነቢዩ መሐመድ (ሰለላ አለይህ ወሰላም) እና የሱፊ ሸኾች የተወለዱበትን ወይም የሞቱበትን ዕለት ለማሰብ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ የነቢዩ መሐመድ የልደት ቀንም ‹‹መውሊድ አን’ነቢ›› ተብሎ በመጠራት በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ የእምነቱ ሥርዓት በድምቀት ተከብሮ ይውላል፡፡

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች

መውሊድ አን” ነቢ በዋናነት የሰደቃን ወይም የምጽዋትን፣ የዱአና የጀባታን፣ የተመረጡ የቁርዐን ክፍሎችንና የመውሊድ ምንባብን፣ የመንዙማ ፕሮግራሞችን አካቶ የሚይዝ ነው፡፡ በሰደቃው ወይም በምጽዋቱ ሀብታሞች ለድሆች ያበላሉ፤ ያጠጣሉ። ያለብሳሉ፡፡ ዱአና ጀባታ ወይም ስጦታ እየተሰጠ የታመመው እንዲድን፣ የደኸየው እንዲከብር፣ መካኑ ልጅ እንዲያገኝ፣ የተራራቀው እንዲቀራረብ፣ የተበደለው እንዲካስ፣ አገር ሰላም እንዲሆን፣ መንግሥት እንዲረጋጋና ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ እንዲሠራ፣ በምረቃና በርግማን ዘለግ ያለ ዱአ ይከናወናል፡፡ በቁርዐንና በመውሊድ ንባብ ክፍለ ጊዜ ከነቢዩ ሙሐመድ ጋር የተያያዙ ነቢዩ የዓለሙ እዝነትና መሪ፣ ለሠናዮች መልካሙን አብሳሪ፣ ለእኩይ ሠሪዎች አስፈራሪ፣ ለሕዝባቸው ሀላልና ሀራሙን አስተማሪ ወዘተ. ሆነው የተላኩ መሆናቸውን በተለይ የሚመሰክሩ የቅዱስ ቁርዐን ክፍሎች ይቀራሉ። ስለ ነቢዩ ሙሐመድ ውልደት፣ በሕይወት በነበሩ ጊዜ ስለ ፈጸሟቸው ገድሎችና ተአምራቶች፣ ስለ ባሕሪያቸው፣በቀደምት ዓሊሞች የተዘጋጁ ‹‹በርዘንጅ›ን› የመሳሰሉ የመውሊድ ኪታቦች መሳጭ በሆነ ስልት ይነበባሉ።

ይህንን ታላቅ በዓል የምናስታውሰው የነቢዩን ትምህርቶች በማሰብ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በማድረግ ጭምር ነው፡፡ ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) ካስተማሩት ትምህርቶች መካከል በተለይም በዚህ ወቅት የሚያስፈልጉንን ጥበቦች ልናነሣቸው ይገባል፡፡ የሀገራችን ማኅበረሰብ በዋናነት የተገነባው በሃይማኖታዊ ዕሴቶች ነው፡፡ የተገነባንባቸውን እነዚህን ዕሴቶች ደጋግመን ባስታወስናቸውና ተግባራዊ ባደረግናቸው ቁጥር ችግሮቻችን እየቀነሱ፣ ሰላምና አንድነታችንም እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡

ነቢዩ መሐመድ ዓለም በአራት ነገሮች ተደግፋ እንደምትኖር ተናግረው ነበር፡፡ እነዚህም፡- የጠቢብ ትምህርት፣ የታላቅ ሰው ፍትሕ፣ የመልካም ሰው ጸሎት እና የጀግና ሰው ተጋፋጭነት ናቸው፡፡ እነዚህ አራት ነገሮች የሀገራችንን ሰላምና ብልጽግና፣ የሕዝባችንን ፍቅርና አንድነት ለመደገፍ በዚህ ሰዓት እጅግ አስፈላጊዎቻችን ናቸው፡፡

የጠቢብ ትምህርት ማኅበረሰብን በዕውቀትና በእውነት ላይ እንዲመሠረት ያደርገዋል፡፡ ከስሜታዊነትና ከጭፍንነት ወጥቶ በአመክንዮና በሚዛናዊነት መርሕ ላይ ያቆመዋል፡፡ ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ጋር አያይዞ እንዲመዝን ያስችለዋል፡፡ ችግርን ተጋፍጦና አሸንፎ በጥበብ እንዲሻገር ያበቃዋል፡፡ ከሰውነት ተራ ወደ አውሬነት እንዳይወርድ፣ ከአእምሮ ሚዛን ወደ ደመነፍሳዊነት እንዳይወርድ ያስችለዋል፡፡

ፍትሕ ከጥቅምና ከወገንተኝነት፣ ከሥልጣንና ከክብር ሳይሆን ከሕግና ከኅሊና እንዲመነጭ ታላቅ ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ‹የታላቅ ሰው ፍትሕ› ያሉት፡፡ ታላቅ ሰው ማለት ለሕግና ለኅሊናው ብቻ የሚታዘዝ ሰው ነው፡፡ ‹ታላቅ ሰው› የሥጋውን ጥቅም ያሸነፈ፣ ለሕጉ ብቻ የወገነ፣ ለእውነት ብቻ የቆመ፣ ለንጽሕና ብቻ የታመነ ሰው ነው፡፡ ፍትሕን ለሕዝባችን ለማረጋገጥ እንዲህ ያለው ሰው ዛሬ ያስፈልገናል፡፡ ፍትሕ በፍትሕ ተቋማትና በተቋማቱ ውስጥ ባሉት ሰዎች ብቻ አይረጋገጥም፤ ተቋማቱን ታላቅ የሚያደርጉ ታላላቅ የፍትሕ ሰዎች ሲኖሩን እንጂ፡፡

ከሕዝባችን መንፈሳዊ ዕሴቶች አንዱ ጸሎት ነው፡፡ ስለ ጸሎት ለኢትዮጵያ ሕዝብ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡ ለዚህች ሀገር ግን ጸሎት ብቻ ሳይሆን የመልካም ሰው ጸሎት ያስፈልጋታል፡፡ በቅንነትና በንጽሕና የሚቀርብ ጸሎት፡፡ ከዘረኝነት፣ ከክፋትና ከግፍ የጸዳ የመልካም ሰው ጸሎት፡፡ ሰላም፣ይቅርታና ፍቅርን ገንዘቡ ያደረገ የመልካም ሰው ጸሎት ዛሬ ያስፈልገናል፡፡

ይህ ወቅት ለእውነት ብቻ የምንቆምበት ጊዜ ነው፡፡ እውነት የሚያመጣውን መሥዋዕትነት ተቀብለን ለእውነት፣ በእውነት የምንቆምበት ወቅት ነው፡፡ ዘመን የወደደውን፣ ጊዜ የወለደውን ሳይሆን እውነት የሆነውን ብቻ የምንናገርበትና የምንሠራበት ወቅት ነው፡፡ ሰዎች ቢቀበሉትም፣ ባይቀበሉትም፣ ወገናችንን ቢያስደስተውም ቢያስከፋውም፣ እውነቱን ተናግረን ከመሸበት ማደር የሚያስፈልገን ወቅት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የጀግና ሰው ተጋፋጭነት ያስፈልገናል፡፡ ጀግና ሰው ማለት እውነትን ይዞ ውሸትን፣ ሐቅን ይዞ ሐሰትን የሚጋፈጥ ነው፡፡

እነዚህ አራት ነገሮች አሉን ወይ? ከአራቱስ የቱ ይጎድላል? ለምን? እያልን ነው ይህንን ታላቅ በዓል ልናከብረው የሚገባን፡፡ በዓሉ የመሰባሰቢያና የፍቅር በዓል ነው፡፡ ታላቁን ከታናሹ ሀብታሙን ከድኻው የሚያገናኝ የፍቅር በዓል ነው፡፡ እንዲህ ባለው በዓል ጊዜ አራቱ ነገሮች ለሀገራችን ያላቸውን አስፈላጊነት ማየት አለብን፡፡ ለበዓሉ በተሰባሰብንባቸው ቦታዎች ሁሉ ስለ አራቱ ነገሮች መነጋገር አለብን፡፡ የጠቢብ ትምህርት፣ የታላቅ ሰው ፍትሕ፣ የመልካም ሰው ጸሎትና የጀግና ሰው ተጋፋጭነት በእኛ ዘንድ አሉ ወይ? መልካም የመውሊድ በዓል፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥቅምት 28 ቀን 2012 ዓ.ም

 

You might also like
Comments
Loading...