Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ መሰረታቸውን ኦሮሚያና አማራ ክልል ካደረጉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አባበ፣ ህዳር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሰረታቸውን ኦሮሚያና አማራ ብሔራዊ ክልሎች ላይ ካደረጉ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ጋር ስብሰባን አካሂደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች በዛሬው እለት ከሰዓት በኋላ ነው በጽህፈት ቤታቸው ያወያዩት።

ስብሰባው የተካሄደው በሁለቱ ክልሎች ህልፈተ-ሕይወት እና የንብረት መውደም የሚያስከትሉ ሁኔታዎች መባባሳቸውን ተከትሎ መካሄዱንም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በሁለቱ ክልሎች በዋናነት እንቅስቃሴ እያካሄዱ የሚገኙ ፓርቲዎች የሕዝቡን ፍላጎት እና የነገ አቅጣጫ ቅየሳ እውን ማድረግ ይችሉ ዘንድ ውይይት ለማስጀመር የታለመ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በውየይቱ ወቅት፥ በዜጎች ላይ አንዳችም ዓይነት ጉዳት ሳያስከትሉ ፖለቲካዊ ተሳትፎን የማካሄድን አስፈላጊነትን አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መሪዎች ሥራቸውን በሚከውኑበት ክልል ሰላምን እና መረጋጋትን ለማስፈን የበኩላቸውን አስተዋጾ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የዛሬው ስብሰባ ባለፉት ሳምንታት በሁለቱም ክልሎች ከሚገኙ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ጋር የተካሄዱት ስብሰባዎች አንድ አካል ነው።

You might also like
Comments
Loading...