Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኔስቴር በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 12፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት መጀመሪያው ሩብ ዓመት በጤናው መስክ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የጤና ሚኔስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክትር ተገኔ ረጋሳ እንደገለጹት፥ በበጀት ዓመቱ የእናቶች ጤናን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህ መሰረትም የቤተሰብ እቅድ አፋጻጸም 67 በመቶ መድረሱን እና የቅድመ ወሊድ ክትትል ላይ ደግሞ 65 በመቶ መሰራቱን አብራርተዋል ፡፡

ከድሬዳዋ አስተዳደር በስተቀር በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በ32 ወረዳዎች እና በ125 የመጀመሪያ ጤና ጣቢያዎች እንዲሁም በ689 ቀበሌዎች በመለኪያው መሰረት መመረጣቸውን ጠቁመዋል።

በዚህም 12ቱ ወረዳዎች 85 ከመቶ በላይ አፈፃጸም ያላቸው ሲሆን፥ 17ቱ ደግሞ 80 ከመቶ በላይ አፈፃፀም ማስመዝገባቸው ተነግሯል።

በሌላ በኩል ከ125 የመጀመሪያ ጤና ክብካቤ አሃዶች 78 የሚሆኑት ከፍተኛ አፈጻጸም ማሳየታቸውን ነው የተናገሩት።

እንዲሁም የማህጸን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት 90 በመቶ የ14 ዓመት ልጃገረዶችን መክተብ እንደተቻለም አስታውቀዋል።

1 ሚሊየን 235 ሺህ 560 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምርመራ እና የምክር አግልግሎት የተሰጣቸው መሆኑ ተመላክቷል።

ምርመራ ካደረጉት ሰዎች ውስጥም 7 ሺህ 790 የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

የገንዘብ እጥረት፣ የግዥ መጓተት እና በአንዳንድ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ ችግር ለስራው እንቅፋት እንደነበርም ተነስቷል ።

በክረምት በተከናወነው የበጎ አድራጎት ተግባር ላይ 150 ሺህ በላይ ሰራተኞች መሳተፋቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በሲሳይ ጌትነት

You might also like
Comments
Loading...