Fana: At a Speed of Life!

የግል ኩባንያዎች የሴት ሠራተኞችን ደህንነትና መብት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የግል ኩባንያዎች የሴት ሰራተኞቻቸውን ደህንነትና መብት የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴሩ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር ከማምረቻው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ምቹ የሥራ ከባቢ በመፍጠር እና በስራ ላይ በሚደርሱ ጉዳቶች ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የፖሊሲ ስፔሻሊስት አቶ ነብዩ መርሻ፣ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ዳምጤን ጨምሮ የመስሪያ ቤቱ እና ከተጠሪ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

በተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት የፖሊሲ ስፔሻሊስት አቶ ነብዩ መርሻ፥ በማምረቻው ዘርፍ ተቀጥረው የሚገኙ ሴቶች በርካታ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በቂ ደመወዝ አለመከፈል፣ ጉልበት ተኮር ስራዎች ላይ ብቻ እንዲሳተፉ ማድረግ እንዲሁም በሚሰሩባቸው ተቋማት ላይ ፆታን መሠረት ያደረገ ህክምና አለማግኘት የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውንም አመላክተዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በቀጣይ ሰፊ ስራዎችን ለመስራት ዕቅድ ይዟል ማለታቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ኢየሩሳሌም ዳምጤ በበኩላቸው፥ መንግስት የማምረቻ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን በርካታ ስራዎች እየሰራ ነው ብለዋል።

የተጀመረው ስራ ግቡን የሚመታው የኩባንያ ባለቤቶች ትርፍ ከማግኘት በዘለለ በድርጅታቸው ተቀጥረው ለሚሰሩ ሴቶች የስራ ላይ ደህንነት እና ጥቅማ ጥቅም ያለ አንዳች መሸራረፍ ማረጋገጥ ሲችሉ መሆኑን አብራርተዋል።

ኩባንያዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ዳይሬክተሯ፥ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የሴቶች የስራ ላይ ደህንነት ብሎም ጥቅማ ጥቅም እንዲረጋገጥ በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

 

You might also like
Comments
Loading...