Fana: At a Speed of Life!

የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ ያስገነባውን የመረጃ ቋት አስመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር አዲስ ያስገነባውን የመረጃ ቋት ባዛሬው ዕለት አስመርቋል።

የመረጃ ቋቱ መገንባት የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን በዘመናዊ የመረጃ ማዕከል በማደራጀት ወጪዋን በራሷ ገቢ የምትሸፍን ሀገር የመፍጠር ራዕይን ለማሳካት የጎላ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል።

በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር የአቅም ግንባታና ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ምህረት ምንአስብ፥መረጃዎችን በአንድ ቦታ (ቋት) በማሰባሰብና በተስማሚ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማደራጀት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የመረጃ አቅርቦትና የመረጃ ልውውጥ ጥራት ያለው፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ግብር ከፋዮችን ከውጣ ውረድና እንግልት በመታደግ ግብራቸውን ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲከፍሉ ያስችላል ነው ያሉት።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለግብር ከፋዮች ምቹ የሆነ የግብር መክፈያ ስርዓት መዘርጋት የሚጠበቅበት በመሆኑ አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ከሚያደርጋቸው ጥረቶች መካከል የመረጃ ቋቱ ግንባታ አንዱ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል።

በሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ማዕከል ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ራሄል ፊደል በበኩላቸው፥ ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የመረጃ ቋት በርካታ ችግሮች እንደነበሩበት አስታውሰዋል።

ስለሆነም የመረጃ ቋትን በዘመናዊ መንገድ የማደራጀት ዓላማን በማንገብ በዘርፉ ልምድና ብቃት ያላቸው ድርጅቶችን በጨረታው በማሳተፍ የመረጃ ቋቱ መገንባቱን ነው የገለጹት።

የመረጃ ቋቱ የእሳት አደጋን የሚከላከል፣ በጣት አሻራ የተደገፈ፣ የደህንነት ካሜራ የተገጠመለት፣ ብልሽቶችን የሚጠቁም፣ የቅዝቃዜና የሙቀት መጠን የሚለካ፣ የውሃና ፍሳሽ መቆጣጠሪያ መሳሪያ የተገጠመለት መሆኑ ተመላክቷል።

መስሪያ ቤቱ ግብር ከፋዮች በዘመናዊና በተቀላጠፈ መንገድ ግብራቸውን እንዲከፍሉ ላመሽቻል ከቴክኖሎጂ ጋር እራሱን እያዘመነ የሚሄድ ረጅም እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like
Comments
Loading...