Fana: At a Speed of Life!

የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህከምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ መካተቱን የጤና ሚኒስቴር ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህከምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ መካተቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህፃንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በትናንትናው እለት፥ የወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስን ተደራሽ በማድረግ የሴቶችና ልጃገረዶች ብሎም የማኅበረሰብ ጤናን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል::

በዚህም የወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ ምርት የህክምና ቁሳቁስ አካል ሆኖ በኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የክትትል ዝርዝር ውስጥ መካተቱን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ የሚመረተዉም ሆነ ወደ ሀገር ዉስጥ የሚገባዉ በብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ መስፈርት ብቻ እንደነበር ሚኒስቴሩ አስታውሰው፤ አሁን ግን የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሱ ወደ ምዝገባ ስርአት ውስጥ ገብቶ ምርቱ ላይ በምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በኩል የደህንነትና የጥራት ቁጥጥር እንደሚያካሂድበትን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር የልጃገረዶችን ጤና ለማሻሻል የሴቶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን ማግኘት ለማይችሉ ልጃ-ገረድ ሴቶች ለማድረስ ዕቅድ መያዙንም ዶክተር መሰረት ዘላለም አክለው ገልፀዋል።

ዶክተር መሰረት፤ ሴቶች በተለይም አፍላ ሴት ወጣቶች ከስነ ተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ ለበርካታ ችግሮች ይጋለጣሉ ያሉ ሲሆን፥ ከነዚህ ችግሮች ዋነኞቹ ከተፈጥሮ የወር አበባ ኡደት ጋር በተያየዘ ንጽህናን በአግባቡ ካለመጠበቅ አንፃር የሚከሰቱ አካላዊ፣ስነልቡናዊና ማህበራዊ ችግሮች ናቸው ብለዋል።

በገጠር ከሚኖሩ አፍላ ወጣቶች መካካል የሚገኙ ልጃገረዶች የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ መረጃና እዉቀት እንዲሁም የሚያስፈልግ ግብአቶችን ባለማግኘታቸዉ ከትምህርት ገበታቸዉ መቅረትና እንዲሁም ለስነልቦና ችግሮች የመጋለጥ እድላቸዉ ከፍተኛ ነው።

ይህንን ችግር ከግምት ዉስጥ በማስገባት የጤና ሚኒስቴር ከሚመለከታቸዉ ሴክተር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት እነዚህን ተጋላጭ ልጃገረዶች በትምህርት ቤት መቆየት እንዲችሉ ለማድረግ የአጭርና የረጅም ግዜ እቅዶች አዉጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

አቅም ለሌላቸው ልጃገረዶች የወር አበባ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በትምህርት ቤት ክሊኒኮች ፣ በጤና ተቋማት በተለይም ከወሊድ በኋላና ከጽንስ ማቋረጥ ጋር ተከትሎ በሚሰጠው የጤና አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት ተደራሸ እንዲሆን ይሰራል መባሉን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

You might also like
Comments
Loading...