Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ሳተላይት የመረጃ መቀበያ አንቴና ግንባታ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የመረጃ መቀበያ አንቴና ግንባታ መጠናቀቁ ተገለፀ።

ኢትዮጵያ የሳተላይት መቆጣጠሪያ እና መረጃ መቀበያ ጣቢያ በእንጦጦ ኦብዘረቫቶሪና ምርምር ማዕከል ውስጥ እየገነባች ትገኛለች።

የዚህ ፕሮጀክት አካል የሆነው የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት የመረጃ መቀበያ አንቴና ግንባታ ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት የገነባው የሳተላይት መረጃ መቀበያ አንቴናው ታህሳስ 7 2012 ዓ.ም ወደ ህዋ የምትመጥቀዋን የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት መረጃዎችን ሙሉ ለሙሉ መቀበል የሚያስችል ነው።

ጣቢያው መረጃዎችን ከመቀበል ባለፈ ሳተላይቶች በአግባቡ ተልዕኳቸውን መፈፀማቸውን ክትትል የሚደረግበት፣ የሳተላይቶች ደህንነትና እንቅስቃሴንም ቁጥጥር የሚደረግበት ነው።

የእንጦጦ የሳተላይት መቆጣጠሪያ እና መረጃ መቀበያ ጣቢያ ፕሮጀክት ከተለያዩ ሳተላይቶች መረጃ መቀበል የሚያሥችል አንቴናና መረጃዎች የሚተነተኑበት የመረጃ ማዕከል ግንባታም እያከናወነ ይገኛል።

ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃ ፍላጎቷን በከፍተኛ ወጪ የምታገኝ ሲሆን፥ ይህንን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለግዢ የሚወጣ የሀገር ሃብት ለማዳን ያስችላል።

የጣቢያው መገንባት በሀገር ውስጥና በአጎራባች ሀገራት ለሚገኙ የሳተላይት መረጃ ተጠቃሚዎች የመረጃ አገልግሎቱን በመሸጥ ገቢ ማስገኘትም የሚያስችል ነው።

ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የመሬትና የህዋ ምልከታ፣ የከተማ ልማት፣ ዓለማቀፍ የተፈጥሮ ሃብትን መቆጣጠር፣ አደጋን መከላከል፣ የካርታ ሥራ፣ ግብርና፣ የደን ልማት፣ ሜትሮሎጂ እና ጂፒኤስ ከሳተላይት ቴክኖሎጂ ትግበራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የተጠናቀቀው የመረጃ መቀበያ አንቴና የሙከራ ስራዎች እየተከናወኑበት እንደሚገኝም የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ቴክሎጂ ኢኒስቲቲዩትን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

You might also like
Comments
Loading...