Fana: At a Speed of Life!

የንግድ ስራ ትርፍ በማያሳውቁ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ ሊወሰድ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር የንግድ ስራ ትርፍ በማያሳውቁ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን በግብር ከፋይነት ተመዝግበው ከሽያጫቸው በታች በሚያሳውቁ እና ግብራቸውን በማያሳውቁ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ ሊወስድ መሆኑን አስታውቋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የታክስ ማጭበርበር ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ እንዳሉት፥ ደረሰኝ በማይቆርጡ እና ዝቅተኛ ሽያጭ በሚያሳውቁ ግብር ከፋዮች ላይ አስፈላጊው መረጃ ተጣርቶና ምርመራ ተደርጎ ተጠናቋል።

በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ድርጅቶች ላይም ሚኒስቴሩ እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።

በሌላ በኩል ሚኒስቴሩ ሀሰተኛ ማንነት አላቸው ብሎ የለያቸው ድርጅቶች ጋር ግብይት ፈጽመው ወጪያቸውን ለማናር በተጠቀሙ ድርጅቶች ላይ ኦዲት የሚደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሚኒስቴሩ በመጀመሪያው ሩብ አመት ከተለዩ ድርጅቶች ተጨማሪ ሀሰተኛ ማንነት ያላቸውን ድርጅቶች ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

አያይዘውም ተቋሙ በህገወጥ ተግባራት ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like
Comments
Loading...