Fana: At a Speed of Life!

የብልፅግና ፓርቲ ምስረታ ሁሉንም ህጋዊ መሰረት የያዘና ህግን ተከትሎ የተፈፀመ ነው- ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ምስረታ ሁሉንም ህጋዊ መሰረት የያዘና ህግን ተከትሎ የተፈፀመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የብልጽግና ፓርቲን አቋምና ምኞት በተመለከተ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በፌስቡክ ገፃቸው መልእክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመልእክታቸውም፥ የብልፅግና ፓርቲን የመመስረት ሂደት በምሁራን ሲጠና መቆየቱን እና በየደረጃው ሁሉም አመራሮች ሲወያዩበት እንደቆዩ አስታውሰዋል።

በትናንትናው እለተም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ባካሄዱት አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ የኢህአዴግ ውህደትን ማጽደቃቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ገልፀዋል።

በዛሬው እለትም የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባዔ እንደሚያፀድቀው ይጠበቃል ብለዋል።

ይህም የፓርቲ ምስረታው ሁሉንም ህጋዊ መሰረት የያዘ እና ህግን ተከትሎ የተፈፀመ መሆኑን ስገልጽላችሁ በታላቅ ደስታ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አክለውም፥ የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራሙን ያሻሻለ መሆኑን፣ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚወስደውን እቅድ የነደፈ እና ይሄንንም ከመላው ህዝብ እና አባላቱ ጋር የሚወያይበትና የሚያዳብረው መሆኑን ገልፀዋል።

“ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና የመውሰድ ህልማችንን እውን የምናደርግበት ትክክለኛው መንገድ የተጀመረ መሆኑን ሳበስር በታላቅ ደስታ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድአንድ ሀይሎች አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ አሃዳዊ ስርዓትን የሚያመጣ፤ የፌደራል ስርዓትን የሚያጠፋ የሚል አሉባልታ ሲናገሩ ይደመጣል ያሉት ዶክተር ዐቢይ፥ ይሁንና በፓርቲው ፕሮግራም ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ህብረ ብሄራዊት፣ ፌዴራላዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚያጠናክርና የሚገነባ እንጂ የማያፈርስ መሆኑን በንግግር ብቻ ሳይሆን በፕሮግራም ጭምር የተካተተ መሆኑን ገልፀዋል።

ሌሎች ፓርቲዎችም ብልፅግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይሆን አማራጭ በማምጣት እንዲሞግቱ እና ለኢትዮጵያ ህዝብም አማራጭ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በመልእክታቸው፥ “የብልፅግና ፓርቲ መሰረት በኦሮሚያ ክልል የቄሮን ትግል፣ በአማራ ክልል የፋኖን ትግል፣ በደቡብ ዘርማና ሌሎች ወጣት አደረጃጀቶች በጋራ ያደረጉትን ትግል ከተረት ተረት ወደ እውነተኛ ብልፅግናና ሰላም፣ ዴሞክራሲ እና አንድነት ለማሸጋገር የተደረገ ሂደት መሆኑ ታምኖ ቄሮዎች፣ ፋኖዎች እና ሌሎችም የወጣት አደረጃጀቶች እንኳን ደስ አላችሁ፤ የታገላችሁበት ፓርቲያችሁ ተመስርቷል፤ ከፓርቲያችሁ ጋር ሆናችሁ ስታነሱት የነበረው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጥረት እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ድርጅቱ የፋኖን እና የቄሮን ትግል የሚያስታውስ የተግባር ማስታወሻ እንደሚያስቀምጥም ለማብሰር እወዳለሁ ሲሉም ገልፀዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባላት ሰሞኑን ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ውስጥ የህግ ልእልናን ለማረጋገጥና ህግ የማስከበር ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ተነስቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰው ሀሳብ ካለው በሀሳብ ገበያ ውስጥ አሳምኖ ስልጣን ከመያዝ ውጪ በሀይልና ትክክል ባልሆነ መንገድ የህዝብን ሰላም የሚያውክ ከሆነ መንግስት ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህግ ልእልናን ለማረጋገጥ አበክሮ ለመስራት መስማማቱንም አስታውቀዋል።

ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ባስተላለፉት መልእክትም “የብልፅግና ፓርቲ ያለብንን ድህነት፣ የዴሞክራሲ እጥረትና የሰላም ችግር በመፍታት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስራ እንዲያገኝ፣ በልቶ እንዲያድር፣ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ የሚተጋ ፓርቲ” መሆኑን በመግለጽ፥ “ይህንን በፕሮግራማችን ላይ በግልጽ ያሰፈረን መሆኑን አውቃችሁ፤ ሌሎች ከእኛ የሚቃረኑ ሀይሎች ካሉ አማራጭ ሀሳብ እያቀረቡ በሀሳብ ልእልና ብቻ ማሸነፍ የሚችሉበትና ሰላማዊ መንገድ የሚከተሉበትን መንገድ እንዲከተሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በመሆን እንዲያረጋግጥ” ጥሪ አቅርበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ ለሰላም፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነት፣ ለእውነተኛ የፌደራል ስርዓት እንዲሁም ለእያንዳንዱ ዜጋ በልቶ የማደር እና ወጥቶ የመግባት ሰላምን የማረጋገጥ ተግባር ለመፈጸም ታጥቆ የተነሳ፣ ግልፅ ፕሮግራም ያለው፤ መጪውን የኢትዮጵያ አቅጣጫ የነደፈ መሆኑን አውቀው የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በሙለታ መንገሻ

You might also like
Comments
Loading...