Fana: At a Speed of Life!

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳዳር ም/ቤት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መስተዳዳር ምክር ቤት ካቤኔ በዛሬው ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በክልሉ ገቢ ግብር እና ታክስ አስተዳደር ረቂቅ ደንቦች እንዲሁም በከተማ ኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄዎች ዙሪያ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡

ካቤኔው የክልሉ የገቢ ግብር እና የታክስ አስተዳደር ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ያጸደቀ ሲሆን÷ ይህም የክልሉ ገቢ አስባሰብና የታክስ አስተዳደር ሥራው በህግና ስርዓት እንዲመራ ከማድረጉ ባሻገር የሚቀርቡ አቤቱታዎችን አሠራሩን ተከትሎ ለመፍታት ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል፡፡

በተጨማሪም በክልሉ የከተማ ኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ ላይ በትኩረት የተወያየ ሲሆን÷ ከዚህ ቀደም በተለይም የክልሉን ህዝብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የኢንቨስትመንት መሬቶች የተሰጡ ቢሆንም ለማልማት በያዙት ውል መሰረት እያለሙ አለመሆኑን ምክር ቤቱ በክፍተትነት አንስቶታል ፡፡

በዚህም መሠረት በከተማ መሬት ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች እድል ተሰጥቶአቸው እና አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ ገብተው የማያለሙ ከሆነ የተሰጣቸው መሬት ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ ገብቶ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የክልሉ መንግስት ካቤኔ አጽንዖት ሰጥቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን በክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በተቀመጠው አሠራር መሰረት በክልሉ በሚገኙ ከተሞች በዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ ላቀረቡ እና መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ ድርጅቶች ቦታው እንዲሰጣቸውና በአስቸኳይ ወደሥራ እንዲገቡ ውሳኔ ማሳለፉን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like
Comments
Loading...