Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ ህዝቡ የሚጠብቀውን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ አገልግሎችን ለመስጠት የሚያስችለው የለውጥ ስራዎች ላይ ነው- ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ህዝቡ የሚጠብቀውን የሰብአዊ መብት አጠባበቅ አገልግሎችን ለመስጠት የሚያስችለው የለውጥ ስራዎች ላይ መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የተቋሙን የ2012 ዓ.ም ዕቅድ በትናንትናው እለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት።

ዶክተር ዳንኤል በዚሁ ወቅት ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ከ15 ዓመታት በላይ ቢሆንም ያለው አደረጃጀት ተልዕኮውን ማስፈፀም የማያስችለው መሆኑን በመግለፅ፤ ለዚህ መፍትሔው ተቋሙን መልሶ ማደራጀት መሆኑን ገልፀዋል።

ለዚህ የሚሆን ጥናት የሀገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታ ባገናዘበ፣ የተለያዩ ሀገሮችን ተሞክሮ በቀመረ እና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የለውጥ ስራው የተቋሙን ማቋቋሚያ አዋጅ ገለልተኛነትና ነፃነት የሚፈትሽ፤ የሰው ሃይል አደረጃጀቱን ተልዕኮ ፈፃሚ የሚያደርግና ወጪ ቆጣቢ ድጋፍ ሰጪ እንዲኖር የሚያስችል፣ የጥቅማ ጥቅም አወሳሰኑ ብቃትና ልምድ ያላቸውን ሰራተኞች ለማቆየት የሚያግዝ፣ እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ እንዲሰጥ በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ከለውጥ ስራው ባሻገር የተለመዱ የመብት ጥሰቶችን የመመርመር፣ አቤቱታዎችን ተቀብሎ የማጣራትና የማማከር ስራዎች በኮሚሽኑ በኩል እየተከናወኑ መሆናቸውም ተመላክቷል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላትም ከሀገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ በዜጎች ሰብአዊ መብቶች ላይ እየደረሱ ያሉ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል ኮሚሽኑ ዝግጁነት ምን እንደሚመስል እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።

ዋና ኮሚሽነሩና የስራ ባልደረቦቻቸው ኮሚሽኑ ይህን ለመስራት የሚያስችል ቁመና እንደሌለው ነው በመግለፅ፤ ለዚህ እንደምክንያት ከቀረቡት መካከል አንዱ የበጀት አናሳነት ነው።

ከተመደበው 74.6 ሚሊዮን ብር መደበኛ በጀት 62 በመቶ ለደመወዝና ለቤት ኪራይ፣ ለመብት ጥሰት መከላከያ ስራዎች 9 በመቶ እና ለምርመራ ስራዎች 12 በመቶ መሆኑ ለማሳያነት በማቅረብ፤ በዚህ ሁኔታ ለህዝቡ ጥያቄዎች ተደራሽ መሆን የማይቻል መሆኑ ነው የተሰመረው።

የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ባይሳ፥ የኮሚሽኑ ዕቅድ ገላጭ መነሻ ሁኔታዎችን እንዲይዝ፣ ቁልፍ ተግባራትን ከአፈፃፀም ሂደታቸው ጋር እንዲካትት፣ ህዝቡ ከተቋሙ የሚጠብቀውን ፍላጎት እንዲያሳይ፣ የአሳታፊነትና የተደራሽነት ጉዳዮችን በሚገባ እንዲመለከቱበት ዕቅዱ ተከልሶ እንዲቀርብ አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ የጀመረውን የለውጥ ስራ በሙሉ ልብ እንደሚደግፍ ያላቸውን እምነት ለተቋሙ የስራ ሃላፊዎች ማረጋገጣቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like
Comments
Loading...