Fana: At a Speed of Life!

ኢ/ር ታከለ ኡማ ለተንቀሳቃሽ ቁሳቁስ ማከፋፋያነት እንዲውሉ የተዘጋጁ ሞዴል ባሶችን ተመለከቱ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተበላሽተው አገልግሎት መስጠት ያቆሙ እና ለተንቀሳቃሽ ቁሳቁስ ማከፋፋያነት እንዲውሉ የተዘጋጁ ሞዴል ባሶችን ተመልክተዋል።

የአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ለረዥም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥባቸው የቆዩ ባሶችን በከተማዋ በሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች አማካኝነት እድሳት እና ጥገና በማድረግ ለወጣቶች የመስሪያ ቦታ እንዲሆን የተዘጋጁ ስድስት ሞዴል ባሶችን ለስራ አጥ ወጣቶች አስረክበዋል።

በቅርቡም ከ400 በላይ የሚሆኑ ያለስራ የቆሙ አውቶቢሶች ተመሳሳይ መልኩ ለተንቀሳቃሽ ማከፋፈያነት በሚያመች መልኩ ጥገና ተደርጎላቸው በየወረዳው ለወጣቶች የሚከፋፈሉ ይሆናል።

እነዚህ ተንቀሳቃሽ ባሶች በዋናነት በቅርቡ ግንባታው ሲጠናቀቅ በሰዓት 80 ሺ ዳቦ ለሚያመርተው የሸገር ዳቦ ፋብሪካ ምርት ማከፋፈያነት የሚውሉ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ለዓመታት ለነዋሪው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት የአንበሳ የከተማ አውቶቢሶች ዛሬም ለነዋሪው ተጨማሪ የመስሪያ ቦታ አማራጭ መፍጠራቸውን የገለፁት ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ በቀጣይነትም የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ያቆሙ ባሶች እድሳት በማድረግ ለወጣቶች አማራጭ የመስሪያ ቦታ እንዲሆኑ እንሰራለን ብለዋል።

የሸገር ዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 95 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በቅርቡም አዲስአበባን እና አከባቢዋን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሌላ ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ እንደሚካሄድም ኢንጂነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል።

You might also like
Comments
Loading...