Fana: At a Speed of Life!

በግጭቶች ተሳትፈዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሰላም ሚኒስቴር ሰሞኑን በሀገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች ተሳትፈዋል በሚል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በየደረጃው ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶች እና ችግሩ ከተፈጠረባቸው አካባቢ አመራሮች ጋር በመሆን ግጭቱ የብሔር መልክ እና የሃይማኖት መልክ ይዞ እንዳይስፋፋ ማድረጉን ገልጿል።

ከብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን እና ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተውጣጡ ግብረ ኃይሎች ለተጎጂዎች እርዳታ እያቀረቡ ነው ብሏል።

በዚህም 878 ኩንታል የምግብ፣ 712 ካርቶን ብስኩት፣ እንዲሁም ምግብ ነክ ያልሆኑ 10 ሺህ 280 የቤት ቁሳቁሶች ተደራሽ መሆናቸውን ነው የተጠቀሰው።

የሰላም ሚኒስቴር በህዝቦች መካከል መተማመን እንዲኖር መጣር፣ የሀሳብ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያና በህግ ስር መፍታት አስፍላጊ መሆኑን ተናግሯል።

ሚኒስቴሩ ሰሞኑን የተከሰተው ግጭት እንዳይባባስ የድርሻቸውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ያበረከቱትን በማመስገን ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማውን ሀዘን ገልጿል።

You might also like
Comments
Loading...