Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የነበሩ የሳይንስ ጥበቦችና ውጤቶችን መመርመርና ማሳደግ የሁሉም ሃላፊነት ነው- ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ሳይንስ ለልማትና ብልፅግና በሚል ርዕስ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉበት የሚገኝ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር÷ የዓለማችን የእድገት ታሪክና ፍጥነት ምክንያት የሳይንስ እና ምርምር ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

የማደግ መንስኤ ሳይንስ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ÷ ኢትዮጵያ ለሳይስንና ስልጣኔ አዲስ አይደለችም፤ ሳይንስን ተጠቅመው የተሰሩ አያሌ ስልጣኔዎችም ያሏት ሀገር ናት ብለዋል፡፡

እነዚህን የቆዩ የሳይንስ ጥበቦችና ውጤቶች ልናውቅ ልናደንቅ ልንመረምርና ልናሳድግ ግዴታና ሃላፊነት አለብን በማለት ተናግረዋል፡፡

ሳይንስ በአጭርና በውስን መልኩ የሚታይ ሳይሆን በስፋትና በርቀት እንድናይ የሚያግዘን ነው በማለት የተናገሩት ፕሬዚዷንቷ ÷ ከዓለም እድገት ተቋዳሽ ለመሆን የሀገር በቀል እውቀትን መሰረት በማድረግ በውጭና በሀገር ውስጥ ያለውን የተማረ የሰው ሃይል መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሳይስንና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም በበኩላቸው÷ የሳይንስና የምርምር ስራዎች ከሌሎች ሴክተሮች ጋር ተቀናጅተው ለተሻለ ልህቀትና ለበለጠ የማህበረሰብን ችግር ለሚፈታ አሰራር የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የቀደመ ፍልስፍና አሰራርን መሰረት በማድረግ ተጨማሪና ያደገ እውቀት አስተሳሰብ በመያዝ ለችግሮች መፍትሄ ይዞ መገኘት ከሳይንስ ባህሪዎች አንዱ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በሳይንስ በኩል በሚገኙ የልህቀት የፈጠራና ውጤታማነት አማራጮች እገዛ ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቅቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመቀላቀል የምታደርገውን ጉዞ በመደመር እሳቤ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ዕይታ የሚቃኝበት እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሳይንሳዊ መሰረት ያላቸው የተለያዩ የአሰራር ለውጦች ማድረጉን የገለፁት ሚኒስትሯ የሳይንስ ባህልን የማዳበር ስራዎችም ተካትተዋል ብለዋል፡፡

የምርምር ጥናቶችና የምርምር ግኝቶች ተበራክተው ለእውቀት ሽግግር አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ ለህትመት እንዲበቁ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሚኒስቴሩ ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን ከሳይስንና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like
Comments
Loading...