Fana: At a Speed of Life!

ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ሀገራዊ አጀንዳ ተነድፎ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ህዳር 4፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ሀገራዊ አጀንዳ ተነድፎ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን የ2012 በጀት ዓመት እቅድና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ወይዘሮ አይሻ መሀመድ፥ በከተሞች ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከልና ህጋዊ የመሬት ይዞታን ለማረጋገጥ፣ ለዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር፣ በአካባቢ ጥበቃ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓትን ለማዘመን እንዲሁም የከተማ ቤቶች ግንባታ ሂደት የእቅዱ ዋና አካል ተደርጎ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በህገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በቤቶች ግንባታ ዙሪያ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን አስመልክቶ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ወይዘሮ አይሻ በምላሻቸው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እና ችግሩ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋጭ የህዝብ ተሳትፎ ተጨምሮበት ህግ በማስከበር ስራው ላይ ሁለንተናዊ ርብርብ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የስራ እድል ፈጠራን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራሮች በሰጡት ምላሽ፣ የአንደኛ ሩብ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ መጀመሪያ በመሆኑ በሁለተኛው ሩብ አመት በርካታ የስራ እድሎችን ለመፍጠር በእቅድ የተያዘ መሆኑን አብራርተዋል።

የከተሞች የቤት ግንባታ ሂደትን በተመለከተ ከአሁን በፊት የነበሩ ችግሮች በጥናትና ምርምር ተለይተው እንዲፈቱ ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ ግንባታቸው እንዲጠናቀቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ በመሆኑ ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ ችግሩ ካልተቀረፈ ሀገሪቱን ወደባሰ ችግር ውስጥ እንደሚከታት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዜጎችን የቤት ዕድል ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር በርካታ ችግሮች እንዳሉ በየጊዜው ብንወያይም ከቃለ-ጉባኤ ግብአት ባለፈ ተጨባጭ መፍትሄ እያመጣን አይደለም ያሉት አባላቱ፥ ኮሚቴው ጠያቂ ሚኒስቴሩ መላሽ እየሆነ መቀጠል የለብንም ብለዋል።

በዚህ ምክንያት በሚፈጠው ችግርም ህብረተሰቡ እየተጎዳ በመሆኑ ሁኔታው በአፋጣኝ መፍትሄ የሚሻው መሆኑን ነው ያሳሰቡት።

በሌላ በኩል መንግስት በስራ እድል ፈጠራው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለበት ሁኔታ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሩብ አመት አፈጻጸም ሲታይ አነስተኛና ዋናው ዕቅድም ከአምናው ጋር ሲነጻፀር መቀነሱ ተመላክቷል።

ከዚህ ባለፈም በመደበኛና በመንግስት ግዙፍ ፕሮጅክቶች የተፈጠረው የስራ እድል ዝቅተኛ መሆኑን አባላቱ ማንሳታቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመንግስት ድጋፎች ፋሲሊቴሽን ስራ እና በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም ውስንነቶች እንዳሉበትም አባላቱ አንስተዋል።

የከተማ ልማት፣ኮንስትራክሽን እና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ ጄ ኢ ጂን ለመተግበር ለሰራተኞች የስነ-ምግባር ስልጠና መሰጠቱን፣ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ከስደት ተመላሾችን መልሶ ከማቋቋም አንጻር የተከናወኑ ተግባራትን በጠንካራ ጎን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በማምረቻውና በግብርና ዘርፎች የስራ እድል ፈጠራው ዝቅተኛ መሆኑን፣ የለማ መሬት አቅርቦት፣ ለኢንተርፕራይዞች የተፈጠረው የገበያ ትስስር፣ በከተማ ፕላን አዘገጃጀት ዙሪያ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ገምግመዋል።

በአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታን በተመለከተም መጓተት እንዳለ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመው በተለይ በ40/60 የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም እና የከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደታየባቸው አስረድተዋል።

በመጨረሻም የሚኒስቴሩ የ2012 በጀት ዓመት የሩብ አመት አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑንና በቀጣይ የበጀት ዓመቱ ወራቶች ቀሪ ስራዎችን በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

You might also like
Comments
Loading...