Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ተጠናቅቋል፡፡

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው መደበኛ ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ባለፋት 6 ወራት በየዘርፉ የተሰሩ ተግባራትና በቀጣይ መሰራት በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡

በዋናነትም የሰላምና ፀጥታ ተግባራት ማጠናከር፣ የፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ የሚታዩ መጓተቶችን መፍታት፣ የትምህርት ዘርፍ ላይ የታዩ ችግሮችን መለየትና መፍትሄ ማበጀት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ምክክር ተደርጓል፡፡

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የገበያ የማረጋጋት ስራን  አጠናክሮ መቀጠል  እና በተለያዩ አካባቢዎች የውሃ የመንገድና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳ ለምክር ቤቱ አባላት ካቀረቡ በኋላም ከምክር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል ።

በጉባኤው በርዕሰ መስተዳድር ርስቱ  የቀረቡ ተሿሚዎች ሹመታቸው በምክር ቤቱ ቀርቦ መጽደቁ ተመላክቷል፡፡

በዚህ መሰረትም አቶ ይግለጡ አብዛ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም  አቶ ዘሪሁን እሼቱ የክልሉ የወጣቶች ስፖርት ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሾመዋል፡፡

በብርሃኑ በጋሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.