Fana: At a Speed of Life!

በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረው አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ ውይይት መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመደመር ጽንሰ ሃሳብ ላይ ያተኮረው አዲስ ወግ አንድ ጉዳይ ውይይት መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሄደ፡፡

በመድረኩ ላይም ምሁራን እና ሌሎች ተጋባዠ እንግዶች ተገኝተው ሀሳብ አስተያየት በመስጠት ውይይት እንደተደረገበት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ፍስሐ ይታገሱ በመድረኩ ላይ፥ የምንመራበት ርዕዮተ ዓለም ከእኛው አውድ ወጥቶ ኢትዮጵያን በምልአት ለመጥቀም የሚችል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

“ከቀደሙ ስርዓተ መንግስቶች አልፈን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ደርሰናል” ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፥ ከአበይት ትኩረቶቹ መካከል የመደብ ቅራኔ ትንታኔ፣ ኢኮኖሚያዊ ቅቡልነት እና አርሶ አደሩን ብቻ መሠረት ማድረግ ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

መደመር ይህንን አካሄድ ለመተካት፤ ግለሰባዊም ሆነ ተቋማዊ ጭቆናን ማስቀረትን፣ ጤናማ ዴሞክራሲያዊ ባህልን በእርቀ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ተሻግሮ መገንባትን አማራጭ እንደሚቃርብም ነው ተናገሩት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መህምር የሆኑት ዮናስ ዘውዴ በበኩላቸው፥ መደመር ለኢትዮጵያ የሚያልመው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ማመቻቸትና አስጠብቆ ማቆየት፣ ያለፉ ስህተቶችን ማረም እና የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ማሟላት መሆኑ ተናግረዋል።

መደመር ከሰብዓዊነት ተፈጥሮ የሚነሳ ሲሆን፥ በመደመር ውስጥ መሰብሰብ፣ ማከማቸት እና ማካበት እንዳሉም ገልጸዋል።

“የቀደሙ ማህበራዊ እሴቶቻችንን መርምሮ ማወቅ፣ ማዳበር ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ወይም የካበተ የአኗኗር ስልት ላይ እንደሚያደርስም አብራርተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፍት ቤት የኢኮኖሚ አማካሪ ማሞ ምህረቱ፥ የመደመር ኢኮኖሚያዊ ግብ ብልጽግናን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በውድድር ላይ የተመሠረተ ነፃ የገበያ ስርዓት በማስፈን እና በቂና አስተማማኝ የሥራ ዕድል በመፍጠር የሚገኝ እንደሆነም ነው የገለጹት።

መደመር ነባራዊው የኢኮኖሚ ሥርዓት ያስገኛቸውን ዕድሎች አስጠብቆ እንደ የእድገት ጥራት እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የመሳሰሉ ህጸጾቹን ለማስወገድ እንደሚሳራም አብራርተዋል።

የብዝሀ ኢኮኖሚ ዘርፎችን ማበራከት፣ የቴክኖሎጂ አቅም በታከለበት ሁኔታ ዕውቀት መር የሆነ ኢኮኖሚን መከተል፣ የንብረት ባለቤትነት መብት እና አስተዳደር የመሳሰሉ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል የመጪውን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት መደመር ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች እንደሆኑም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የውጪ ግንኙነት መሠረቱ የሀገር የሕልውና ጥያቄ ሲሆን፥አግባብ ባለው መልኩ ማስተናገድ ካልተቻለ አሉታዊ ውጤቶችን ሊያስከትል እንደሚችልም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ በቀጣና፣ በአህጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አበይት ሚናን ስትጫወት ኖራለች።

መደመር ከውጪ ግንኙነት አንጻር ጎረቤት ሀገራትን የሚያስቀድም ሲሆን፥ ቀጣና ሰላም ሳይሆን ሀገር ሰላም እንደማትሆንም ተጠቁሟል።

መደመር ታሪካዊ እሴቶቻችንን አስቀጥሎ መግባባት እና ትብብር ላይ ትኩረት በማድረግ ብሔራዊ ክብርን ለማስጠበቅን ያለመ መሆኑም ነው በውይይቱ የተነሳው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.