Fana: At a Speed of Life!

ግብርን በወቅቱ በማያሳውቁ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል-የገቢዎች ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት11፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የገቢዎች ሚኒስቴር ግብርን በወቅቱ በማያሳውቁ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ ኡሚ አባጀማል ጉዳዩን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ  ሰጥተዋል።
ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው ግብርን በወቅቱ አለማሳወቅ ማለት  ነጋዴዎች በታክስ ህጎች በተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የታክስ ማሳወቂያ በማቅረብ በሕጉ የተጣለባቸውን ግዴታ አለመወጣት መሆኑን አብራርተዋል።

ነጋዴዎች  የትርፍ ገቢ ግብር በየዓመቱ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደግሞ በየወሩ የታክስ ማስታወቂያ በመሙላት ለታክስ አስተዳደሩ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

የታክስ ማስታወቂያ ካልቀረበ ተቋሙ በማንኛውም ጊዜ የሚያገኘውን ማስረጃ መሠረት ታክስ ከፋዩ ሊከፍል የሚገባውን ታክስ በግምት በማስላት ታክስ የሚወሰን መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም ግብርን በወቅቱ የማያሳውቅ  ነጋዴዎች ከሚያጋጥማቸው ተጠያቂነት፣ አስተዳደራዊ ቅጣት እና አላስፈላጊ መጉላላት ለመዳን በተሰጣቸው እድል ተጠቅመው የሚጠበቅባቸውን ግዴታ መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ግብራቸውን በወቅቱ ያላሳወቁ ግብር ከፋዮች በዘገዩበት እያንዳንዱ ጊዜ ያልተከፈለው ታክስ ላይ ከ5 በመቶ ጀምሮ 25 በመቶ አስኪሞላ ድረስ ቅጣት ይከፍላሉ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ።

ግብር የሚያጭበረብሩ ድርጅቶች ላይ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና ከብሔራዊ ደህንነት እና መረጃ አገልግሎት ጋር በቅንጅት  በመስራት እርምጀ እየተወሰደ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ኡሚ፥  በቀጣይ የተሰጣቸውን  እድል ተጠቅመው ግብር በማያሳዉቁ ድርጅቶች  ላይ ጠንካራ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛውም ነጋዴ ወቅቱን ጠብቆ የሚጠበቅበት ግብር የማይከፍል ከሆነም ሀብት እና ንብረት በመያዝ የመንግስት ገቢ እንዲሰበሰብ የሚደረህግ መሆኑን ጠቁመዋል።

You might also like
Comments
Loading...