Fana: At a Speed of Life!

የኢህአዴግ ውህደት በምሁራን ዕይታ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢህአዴግ ውህደትን በተመለከተ ኢህአዴግ ራሱን ጨምሮ የተለያዩ የድጋፍ እና አስፈላጊ አይደለም የሚሉ ሀሳቦች እየተስተናገደበት ይገኛል።

በኢህአዴግ ግንባር እና አጋር ድርጅቶች የታሰበው በውህደት አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የመመስረት ጉዞ በተለያዩ አመለካከቶች የተለያዩ ጽንፎች ላይ የቆመ ይመስላል።

ሀሳቡን በሚቀበሉት እና እንደ ግንባሩ አዲስ ውህድ ፓርቲው የብሄራዊ ድርጅቶቹን ጠርዝ የለቀቀ አካሄድ ፈር በማስያዝ እና ልዩነቶችን በማጥበብ ወደ አንድ ያመጣቸዋል የሚል እምነት አላቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ ህብረ ብሄራዊ በሆነች ሀገር መሰል እንቅስቃሴዎች መፍትሄን ሳይሆን በክፉ ችግሮች የሚገለጡ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል መደምደሚያዎች ይደመጣሉ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ውህድ የሚለውን መንገድ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሊገቡበት ስለመቻላቸው መሆኑን ያነሳሉ።

በጥቅሉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች በማለት የሚከፍሉት ዶክተር ተመሰገን የህብረተሰቡ ንቃተ ህሊና እያደገ እና እየተቀየረ መምጣትም እንደ መነሻ ምክንያት ይነሳል ባይ ናቸው።

ስለዚህ ከሩብ ምዕተ አመት በላይ ያስቆጠረው የግንባር ጉዞ በእነዚህ ጉዳዮች አስገዳጅነት ወደ ውህደት እያመራ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ውህደት አንድ ጠንካራ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረግ እና ፓርቲው የውስጥ ዴሞክራሲውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ በዚህ ውሳኔ ላይ ስለመድረሱም አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶክተር ፍርዲሳ ጀቤሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያን በሚመስሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች፥ የተለያዩ ማንነቶችን ይዘው በሚኖሩባት ሃገር መሰል አካሄዶች ተቀባይነት የላቸውም ይላሉ።

እነዚህ እና መሰል ችግሮች ደግሞ ህዝቡ የጋራ ራዕይ እንዳይኖረው እና አንዱ አንዱን እንዲጠራጠር ሁኔታዎችን ያመቻቻሉም ነው የሚሉት።

ጉዳዩንም ህዝቡ እንዲረዳ ፓርቲው በተሞክሮነት እየተጠቀመባቸው ያሉት የህንድ እና ታንዛኒያን የመሳሰሉ ሀገራት ከኢትዮጵያ ታሪክ እና አሁናዊ ሁኔታ ጋር የማይመሳሰል ነው ብለዋል።

ዶክተር ተመስገን ደግሞ የኢህአዴግ ግንባር ድርጅቶች አንድ አቋም አለመያዝ ብዙም ችግር እንደማያመጣ ጠቅሰው፥ አንድ ፓርቲ ቅርጹን በመቀየር ሂደት የአስተሳሰብ ለውጦችም ስለሚከተሉ መሰል የሀሳብ አለመግባባቶች እየተቀረፉ የመሄዳቸው እድል ሰፊ ስለመሆኑ ያስረዳሉ።

ዶክተር ፍርዲሳ ውህደቱ የዴሞክራሲን ጽንስ ሀሳብ የሚደፈጥጥ በመሆኑ በህዝቦች ላይ ችግር ይፈጥራል ባይ ናቸው።

ይህ ደግሞ የህዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚገፍ አሰራር ስለሚሆን የህዝብ ወሳኝነትን ወደጎን በመተው የግለሰቦች አላማ ማስፈጸሚያ ይሆናል በሚል ይከራከራሉ።

ባለፉት ጊዜያት የፓርቲ እና መንግስት ተቀላቅሎ መቅረብ እና መታየት ከፈጠራቸው ትልልቅ ችግሮች መካከል ሁሉንም ነገሮች ፓርቲዎች እየተገበሩ የሚቀጥሉ እንደሆኑ እንድናስብ አስገድዶናል የሚሉት ደግሞ ዶክተር ተመስገን ናቸዉ።

በውህደት ውስጥ ፌደራሊዝምን በተጠናከረ መልኩ ለመተግበር የሚሰራበት እንጂ ለማጥፋት አይደለም ያሉት ዶክተር ተመስገን፥ ፍላጎቱ ያለው አካል ቢኖር እንኳን ህገ መንግስቱ እንደማይፈቅድለት ያስረዳሉ።

ውህደቱ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት በኢህአዴግ ውስጥ አንዱ የፓርቲው ሙሉ አባል ሌላኛው ደግሞ እንደ ሁለተኛ ዜጋ አጋር እየተባለ የሚሄድበትን አካሄድ ለማስቀረት ታስቦ መሆኑ ይነገራል።

ይህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሀገሩ እኩል መሆኑን እና የሁሉም ዜጋ ርብርብ ለሀገሪቱ የወደፊት ጉዞ አስፈላጊ መሆኑን ለማመላከት በማሰብ ነው።

ዶክተር ፍርዲሳ አንዱን አጋር ሌላውን አባል አድርጎ መቀጠሉ ተገቢ እንዳልነበር አውስተው፥ ይህን በውህደት ሳይሆን በቀላሉ ማስተካከል እንደሚቻል ያነሳሉ።

በጥቅሉ የኢህአዴግ ውህደት የቡድንን መብት በመጋፋት ለግለሰቦች ብቻ መብትን የሚያጎናጽፍ መሆኑንም ነው ዶክተ ፍርዲሳ ያብራሩት።

ውህደቱ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ዜጎች በእኩል ደረጃ ያላቸውን በማዋጣት እንዲሄዱ የሚያደርግ መስመር ስለመሆኑ ደግሞ ዶክተር ተመስገን ይናገራሉ።

በአካሄዱም የቡድን እና የግል መብት በእኩልነት የህግ ከለላ የሚደረግለት ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በአጠቃላይ ከውህደቱ አንድነትን፣ ለጋራ ግብ መስራትን፣ ድርጅታዊ ጥራት፣ አሳታፊነትን፣ የሁሉም ጉዳይ ያገባኛል ባይነትን ማትረፍ እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።

የውህደቱ የመጨረሻ ግብ መደመር አሳክቸዋለሁ ከሚላቸው እና መሰረት ካደረጋቸው የመሰባሰብ፣ መልካምን ይዞ የመቀጠልና ከስህተት የመማር መርሆዎች ጋር የሚዛመድ መሆኑንም ነግረውናል።

 

 

በአፈወርቅ አለሙ

 

 

You might also like
Comments
Loading...