Fana: At a Speed of Life!

የአንድነት ፓርክ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤተ መንግስት ግቢ የተሰራው የአንድነት ፓርክ በዛሬው እለት በይፋ ተመረቀ።

በፓርኩ ምረቃ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት እና የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ተወካዮች እና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

እንዲሁም የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች እና ምክትል ርእሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለአንድነት ፓርክ ግንባት መሳካት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉም አካላትና ባለሃብቶች ምስጋና አቅርበዋል።

ታላቂቷን ሀገራችን እንደ ስሟ ታላቅ ለማድረግም ሁሉም ዜጋ የባለሃብቶችን ስራ እንደ አርአያ በመውሰድ በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

ፓርኩ በዙ ይናገራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ፥ በሀገራችን ተከስተው የነበሩ አኩሪና የሚያሳፍሩ ታሪኮች የተንጸባረቁበት መሆኑን አስታውሰዋል።

የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ማንኛውም ሀገር የራሱ ታሪክ ያለው መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንት ኬያንታ፥ ለወደ ፊት የተሻለ ሀገር ግንባታም ካለፉት ታሪኮች ውስጥ ጥሩ ተሞክሮዎችን መውሰድ እንደሚገባ አንስተዋል።

ኬንያ እና ኢትዮጵያ በባህል፣በኢኮኖሚ እና በተለያዩ ዘርፎች ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከርም በቅንጅት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያካሄደቸው ያለው ሁለንተናዊ ለውጥ የሚበረታታ መሆኑም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጠቁመዋል።

የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በበኩላቸው ምርቃቱን አስመልክተው ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ሁለንተናዊ ግንኙነት ያላት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር፥ ለዚህም በደቡብ ሱዳን በተከሰተው የሰላም ችግር ወቅት ኢትዮጵያ በርካታ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን በመቀበል ያደረገቸውን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል ሰላም እንዲወርድ ያደረገችውን ከፍተኛ ጥረትም አድንቀዋል።

የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ የተከናወነው የቤተ-መንግሥት ዕድሳት አስደናቂ መሆኑን በመግለፅ ለሀገሪቱ ቱሪዝም እንዲሁም የኢኮኖሚ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የአንድነት ፓርክ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማስፋፋት እና ቱሪዝምን በመሳብ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለውና የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በዚህ በፕሮግራም ላይ በመገኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውን በመግለፅ ለኢዮጵያ መንግስትና ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያ በሱዳን ተፈጥሮ የነበረውን ቀወስ ለመፍታት የነበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አብደላ ሃምዶክ፥ የአንድነት ፓርክ ለሀገሪቱ ታላቅ ስጦታ መሆኑን አንስተዋል።

በምርቃት ስነ ስዓቱ ላይ ለአንድነት ፓርክ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት የዕውቅና ሰርተፊኬት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተቀብለዋል።

በዛሬው እለት የተመረቀው የአንድነት ፓርክ የመደመር እሳቤ ማሳያ ነው ብሏል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት።

በዛሬው እለት የተመረቀው የአንድነት ፓርክ ከነገ ጀምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ለጎብኚዎች ክፍት የሚደረግ ይሆናል።

በዚህም መሰረት በነገው እለት የመከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ አባላት በቤተ መንግስት ግቢ የተሰራውን የአንድነት ፓርክ የሚጎበኙ ይሆናል።

ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ በእድሜ ታላላቅ ዜጎች እና የጎዳና ተዳዳሪዎች ቤተ መንግስቱን እንደሚጎበኙም አስታውቀዋል።

ከስኞ ማለትም ከጥቅምት 3 2012 ጅምሮ ማንኛውም ዜጋ 200 ብር እንዲሁም በቪአይፒ (VIP) 1 ሺህ ብር በመክፈል ቤተ መንግስቱን መጎብኘት እንደሚችልም ተገልጿል።

You might also like
Comments
Loading...