Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀን ወደ ህዳር 10 ተዘዋወረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሲዳማ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀን ወደ ህዳር 10 2012 ዓ.ም መዘዋወሩን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ከዚህ ቀደም ቦርዱ የህዝበ ውሳኔው የድምፅ አሰጣጥ ህዳር 03 2012 ዓ.ም ይካሄዳል ብሎ የነበረ ሲሆን፥ በዛሬው እለት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ግን ህዝበ ውሳኔ ድምጽ መስጫ ቀን ሽግሽግ መደረጉን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫው፥ ቦርዱ ህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም በከፍተኛ ትጋት እየሰራ እንደሚገኝ እና የደቡብ ክልል ምክር ቤትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በተመሳሳይ ሁኔታ እየሰሩ እንደሆነ እንደሚያመን አስታውቋል።

በመሆኑም ያልተጠናቀቁትን ተግባራት በተለይ የአስፈጻሚዎች ምልመላ ስራ እና የሚጠበቁት ህጋዊና አስተዳደራዊ ማእቀፎች ተጨማሪ ቀናት የሚፈልጉ በመሆኑ ሂደቱ ላይ የቀናት መሸጋሸግ አስከትሏል ብሏል።

በዚህም መሰረት የድርጊት መርሃ ግብሩ ተክለሶ ህዝበ ውሳኔው የሚከናወንበት ቀን ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን መወሰኑን ነው ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔን አፈጻጸም ሂደት አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔን ለማስፈጸም አስፈላጊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

ለሂደቱም ቦርዱን ጨምሮ ከሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር ተግባራትና የጊዜ ሰሌዳ የሚያሳይ የድርጊት መርሃ-ግብር ማውጣቱ ይታወሳል።

በድርጊት መርሃ-ግብሩ መሰረት ቦርዱ የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውን ቆይቷል፤ እስካሁን ከተከናወኑት ዋና ዋና ተግባራት መካከል፣ በጀትን እንዲሁም መከናወን አለባቸው የተባሉ ሌሎች ተግባራትን አስመልክቶ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እንዲሁም የሲዳማ ዞን አመራር አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶች ማካሄድ።

ጸጥታንና የምርጫ ደህንነትን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል የጸጥታ እና የህግ አስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይቶችን ማድረግ።

የበጀት እቅድ ማዘጋጀትና እና ለቦርዱ የባንክ ሂሳብ መግባቱን መከታተል፣

የህዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣

ምርጫ ምልክቶችን መምረጥና ማስወሰን እንዲሁም ይፋ ማድረግ፣

የምርጫ ማስፈጸሚያ፣ ቅጾች እና የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ዲዛይን እና ህትመትን ማጠናቀቅ፣

ለአፈጻጸሙ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችና ቁሳቁሶች ግዥን ማከናወን፣

የህዝበውሳኔው አፈጻጸም ሂደት በቂ ታዛቢዎች የተሳተፉበት እንዲሆን ለማድረግ ከሲቪል ማህራት ጋር በጋራ መስራት፣

የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን ምልመላ ማከናወን የመሳሰሉት ናቸው።

በድርጊት መርሃ-ግብሩ መሰረት ከክልሉና ከሲዳማ ዞን አመራር አካላት ጋር በተደረገ ስምምነት የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት ለማረጋገጥ፣ ሂደቱን የተቀላጠፈ ለማድረግ፣ አግባብ ያለው የሃብት አጠቃቀም እንዲኖር ለማስቻል እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበሩ መልካም ተሞክሮዎች ላይ መሰረት በማድረግ አስፈጻሚዎች ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከአዲስ አበባ ዙሪያ እንዲመለመሉ ተወስኖ ወደተግባር ተገብቷል።

ነገር ግን የታቀደውን ያህል ቁጥር አመልካች ሊገኝ ባለመቻሉ ቦርዱ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአንድ የምርጫ ጣቢያ የሚፈለጉትን የአስፈጻሚዎችን ቁጥር ወደሶስት በመቀነስ በአጠቃላይ የሚያስፈልገውን የአስፈጻሚዎች ቁጥር 5500 ያደረገ ሲሆን ተፈላጊው ቁጥር ያላቸው ገለልተኛ እና ብቁ የምርጫ አስፈጻሚዎችን የመመልመል ስራን ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በፍጥነት ለማጠናቀቅ እየሰራ ይገኛል።

ይህም የአስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት ከማረጋጡም በተጨማሪም ሃብትን በአግባቡ ለመጠቀምና ስራውን በታቀደለት ጊዜ ለማከናወን ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ያምናል።

ህዝበ ውሳኔውን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ውይይት በበጎ መንፈስ የቀጠለ ሲሆን በታቀደው መሰረት የሚመለከታቸው የጸጥታና የአስተዳደር አካላት ዝርዝር የምርጫ ደህንነት እቅድ አጠናቅቀው አቅርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት የህዝበ ውሳኔውን ሂደት የሚያስተባብር የፕሮጄክት ጽህፈት ቤት ያቋቋመ ሲሆን፣ ክልሉም ለህዝበውሳኔው የሚያስፈልገውን ሙሉ በጀት በቦርዱ የባንክ ሂሳብ ገቢ አድርጓል።

ቦርዱ ከዚህ በፊትም እንዳሳወቀው ህዝበ ውሳኔው የሲዳማን ክልልነት ካረጋገጠ ስለሃዋሳ ከተማ እጣፈንታ እና የሃብት ክፍፍል እንዲሁም በዞኑ የሚኖሩ የሌሎች ብሔረሰብ አባላት ጥበቃን አስመልክቶ የሚወጡ ህጎችና የአስተዳደር ማእቀፎች የጊዜ ሰሌዳ አስመልክቶ ውይይቶች ተደርገዋል።

በውይይቶቹ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለማጠናቀቅ እስከ መስከረም 30 ድረስ ጊዜው እንዲራዘም ከውሳኔ ላይ የተደረሰ ቢሆንም እስካሁን እነዚህ ተግባራት ተጠናቅቀው አልቀረቡም።

በተጨማሪም በቦርዱና በሚመለከታቸው አካላት መካከል ነሃሴ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በተደረገው ውይይት የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔው የሚካሄድባቸው ቀበሌዎችን ዝርዝር ለመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርብ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም እንዲሁም በተከታይ ከቦርዱ ማሳሰቢያ ቢላክም ህዝበውሳኔው የሚካሄድባቸው ቀበሌዎች ዝርዝር እስካሁን ድረስ አልቀረበም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝበ ውሳኔውን ለማስፈጸም በከፍተኛ ትጋት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የደቡብ ክልል ምክር ቤትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በተመሳሳይ ሁኔታ እየሰሩ እንደሆነ ያምናል፡፡ በመሆኑም ያልተጠናቀቁትን ተግባራት በተለይ የአስፈጻሚዎች ምልመላ ስራ እና የሚጠበቁት ህጋዊና አስተዳደራዊ ማእቀፎች ተጨማሪ ቀናት የሚፈልጉ በመሆኑ እና ሂደቱ ላይ የቀናት መሸጋሸግ አስከትሏል።

በዚህም መሰረት የድርጊት መርሃ ግብሩ ተክለሶ ህዝበ ውሳኔው የሚከናወንበት ቀን ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲሆን ወስኗል።

ቦርዱ በቀሩት የህዝበውሳኔው ዝግጅት እና ማስፈጸም ሂደቶችም የሚመለከታቸው አካላት የዘገዩትን ተግባራት አከናውነው እንደሚያጠናቅቁ ባለሙሉ ተስፋ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

You might also like
Comments
Loading...