Fana: At a Speed of Life!

ሀገራዊ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ነፃና ተአማኒ እንዲሆን በቅንጅት ይሰራል-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተያዘው በጀት ዓመት የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ እና ተአማኒነት ባለው መልኩ እንዲካሄድ መንግስት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ የጋራ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የ2012 የበጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች የተካተቱበት የመክፈቻ ንግግር አቅርበዋል።

ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው በተያዘው በጀት ዓመት ያለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እንዲተገበር ጥረት የሚደረግበት መሆኑን አንስተዋል።

ያለፈው ዓመት በፖለቲካ፣ በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ በፍትሕ ሥርዓት እና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የነበረውን ሀገራዊ ጉድለት ማስተካከል የጀመርንበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፥ ይሁን እንጂ ጉድለቱን በተሟላ ሁኔታ ያቃናንበት ደረጃ ላይ አልደረስንም ብለዋል።

በሌላ በኩል አንዳንዶቹ በባህሪያቸው መዋቅራዊ በመሆናቸው ከአንድ ዓመት አለፍ የሚል ምክንያታዊ ጊዜን የሚጠይቁም መሆናቸውን አንስተዋል።

2012 ዓ.ም የለውጡን ጉዞ የተሻለ መሠረት የምናስይዝበት ይሆናል ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ይህም ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የመደመርን እሳቤ መሠረት አድርጎ የሚጓዝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዚህ መሰረትም በሀገሪቱ የነበሩ መልካም የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድሎችን ጠብቆ ማስፋት፣ ባለፉት ዘመናት የተሠሩ ስህተቶችን ማረምና የመጪውን ትውልድ ፍላጎትና ጥቅም የማሳካት ስራዎች በትኩረት ይሰራባቸዋል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ ያለፈችባቸው የታሪክ ምዕራፎች መልካም ፀጋዎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ስህተቶችም ያሉ መሆኑን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቷ፥ እኩልነትን፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን፣ አካታችነትን፣ የሰብአዊ መብት አያያዝን፣ የፍትሕ ሥርዓት መዛነፍን በተመለከተ የተፈጸሙ ስህተቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በቅርብ ታሪካችን እንኳን ልዩነቶቻችን ላይ የሠራነውን ያህል አንድነታችን ላይ አልሠራንም፤ የኢኮኖሚ እድገቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚገባው ልክ አላረጋገጠም፤ በሰብዓዊ መብት አያያዛችንና በፖለቲካዊ መብቶቻችን ላይ ሰፊ ጉድለቶች ተመዝግበዋል ብለዋል በንግግራቸው።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የሰላም ግንባታን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት የተሰደዱትን ማስተናገዷን የቀጠለችውን ያህል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ተፈናቃይ የሆኑበትን አሳዛኝ የታሪክ ገጽ አስታውሰዋል።

ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትን የህጋዊ ማዕቀፎችና አቅሞችን በማዳበርና በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ አሁን በሀገራችን ያለውን አንጻራዊ ሠላም ወደ አስተማማኝ ሠላም ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በቀጣይ ሀገሪቱ የምታስተናግዳቸው ሀገራዊ ምርጫ እና ሌሎች ክስተቶችን ሠላማዊ በሆነ መልኩ ለመፈጸም የሚያስችል አቅም ለመፍጠር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ብሎም ለማጠናከር የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፤ ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የማኅበረሰብ ልማት ፕሮግራሞችም የሚካሄዱ ይሆናል ነው ያሉት።

በተያዘው ዓመት የሚካሄደው ምርጫም በተቻለ መጠን ባለፉት ምርጫዎች ያጋጠሙንን ግድፈቶች በሚያርም መልክ እንዲከናወን፣ ነጻና ዴሞክራያዊ ሆኖ ተአማኒና ተቀባይነት ያለው እንዲሆንና የፖለቲካ ልሂቃንንና የምልዓተ ሕዝቡን ተሳትፎ ያረጋገጠ እንዲሆን መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሰራል ነው ያሉት።

የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻልን በተመለከተም ህዝቡ ወደ ፍርድ ቤቶች የሚያቀርበውን ከፍተኛ የአገልግሎት ጥያቄ ለመመለስ የሚያሥችል በዓመት እስከ 250 ሺህ መዛግብት ለማስተናገድ የሚያስችል አወቃቀር ይፈጠራል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መምሪያ፣ የቁጥጥርና ክትትል ክፍሎችን በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋም እና ማደራጀት፣ ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓትን ማጠናከር፣የዳኝነት አገልግሎት ሥራ ደጋፊ የሆኑትን የአስተዳዳር አካላት ውጤታማነት ማረጋገጥ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢኮኖሚውን በተመለከተም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን በማስታወስ የተጀመረው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ለወጣቶችና የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና የማፈላለግ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ተናግረዋል።

ወጣቶች ለሥራ ዲሲፕሊን የሚበቃቸውን ሥልጠና ወስደው በሚሰማሩበት ዘርፍ ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው እንዲሰሩም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ኮንትሮባንድ፣ ታክስ ማጭበርበርንና ታክስ መሰወርን፣ እንዲሁም በህቡዕ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት በማምጣት ኢኮኖሚውን ወደ ተሻለ ጤንነት የማሸጋገር የተቀናጀ ሥራ የሚከናወን መሆኑንም አክለዋል።

የ2010/2011 ዓ.ም ምርት ዘመን የሰብል ምርትን 406 ሚሊየን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ 316 ሚሊዮን ኩንታል ማለትም 78 በመቶ ማድረስ ተችሏል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፥ ይህም በ2009/2010 ዓ.ም ከተመረተው 267 ሚሊየን ኩንታል ጋር ሲነፃፀር የ4 ነጥብ 29 በመቶ እድገት ማሳየቱን አንስተዋል

ሀገራዊ የማዳበሪያ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታትና በዓመት ከግማሽ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት አዲስ የማዳበሪያ ፋብሪካ ድሬዳዋ ላይ ለማቋቋም ከአንድ የውጭ ኩባንያ ጋር ሽርክና የመፈራረም ሥራው በቅርቡ የሚጀመር መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፍም በበጀት ዓመቱ በገጠር ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ የውሃ ተቋማት ግንባታና ከ13 ሺህ በላይ የማይሠሩ ተቋማትን መልሶ የማቋቋም ሥራ የሚከናወን መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በከተማ ደግሞ 60 የመጠጥ ውሃ ተቋማት ጥናቶችን፣ 60 አዳዲስ ግንባታዎችንና 30 የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን ለማካሄድ ታቅዷል ነው ያሉት።

በኤሌክትሪክ ሀይል ዘርፍም፥ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በግንባታ ላይ ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው እንዲፋጠን ይደደራጋል ያሉት ፕሬዚዳንቷ ፥በተጨማሪም በመንግስትና በግል አጋርነት የሚሠሩት 10 ፕሮጀክቶች ሥራቸው ይጀመራል ብለዋል።

የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቱን ከማስፋትና ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ በ405 የገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮች አንድ ሚሊየን ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አመላክተዋል።

የትምህርት ዘርፉን ለማሻሻልም ጥራት ያለው ትምህርትና ሥልጠና በሁለም ደረጃዎች ማስፋፋት እንዲቻል በ2012 ዓ.ም የተጀመረውን የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ወደ ተግባር የማስገባት ስራ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተጀመረው ረቂቅ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ እንዲሁም የትምህርት ሕግም ተጠናቆ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግና ብሎም የጾታ እኩልነት ማረጋገጥ ረጅም ጉዞ ላይ ከፍተኛ ቦታ የሚይዝ ግኝት በ2ዐ11 ዓ.ም መመዝገቡን ያሰታወሱት ፕሬዚዳንቷ፥ ይህንን በመጠቀም በ2ዐ12 ዓ.ም እነዚህ ግኝቶች ጽኑ መሠት እንዲኖራቸውና እንዲሰፉ የማድረግ ተግባር ይከናወናል ብለዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደግ አንፃርምን በ2012 በጀት ዓመት በባሕል ዘርፍ፣ ለእደ ጥበብ ዘርፍ፣ የአቅም ግንባታና የገበያ ትስስርር ሥራ ለመሥራት፣ ኪነ ጥበብ ለሀገር ሠላም ግንባታ የሚውልበትን አሠራር ዘርግቶ ለመተግበር መታቀዱን ጠቁመዋል።

ከቅርስ ጥገናና እንክብካቤ አንፃር የላሊበላ፣ የአክሱም፣ የአባ ጅፋርና የጎንደር አብያተ መንግሥት ቅርሶች ጥገና ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በመከተሏ በተለያዩ ሀገራት በእስር እና በእንግልት ላይ የነበሩ ከ90 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሥራ ሥምሪት ስምምነቶችን መደራደርና ከተወሰኑት ጋር ስምምነት ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ከኤርትራ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነትና የአየር ትራንስፖርት የተጀመረ መሆኑን በመግለፅ፥ የተመሰረተው ግንኙነት በሕጋዊ ማዕቀፎች እንዲመራ ለማድረግ ድርድርና ውይይት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል ፕሬዚዳንቷ።

በምናያቸው አስደሳች ነገሮች እንደምንደሰተው ሁሉ በዚህ ሀገር የሚሆነውን ክፉ ተግባር መጠየፍ፣ተመልሶም እንዳይደገም አስተዋጽኦ ማበርከት የፍላጎት ጉዳይ ሳይሆን በግድ ልንሳተፍበት የሚገባ የሀገር ግንባታ ጉዞ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የሁሉም ዜጋ ራስ ምታት መሆን አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ኢትዮጵያውያን አባቶችና እናቶች ያስተማሩንን የሰብዓዊነት፣ የመደጋገፍ እና ችግርን በደቦ የማሸነፍ መልካም እሴታችን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።

You might also like
Comments
Loading...