Fana: At a Speed of Life!

ከጥንቅሽ ወለላ ጭማቂ ለማዘጋጀት የሚያስችል መሳሪያ ለማምረት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከጥንቅሽ ወለላ ጭማቂ ለማዘጋጀት የሚያችለውን መሳሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት የዲዛይን ስራ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ድጋፍ በመልካሳ ግብርና ምርምር የነገሌ ንኡስ ቅርንጫፍ ተመራማሪነት ሲሰራ የቆየው ከጣፋጭ ማሽላ አገዳ ጭማቂ የማምረት ምርምር እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል።

ማዕከሉ ለአካባቢው አየር ንብረት ተስማሚ የሆነ የማሽላ ዝርያን እያላመደ እንደሚገኝም ተመላክቷል።

በምርምር የተገኘውን ዝርያም ወደ አርሶ አደሩ በማሰራጨት ተጠቃሚ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በዋና ተመራማሪው  ዶክተር ፋንታሁን ወልደሰንት  የሚመራው ምርምሩ አርሶ አደሮች እምብዛም ከማይጠቀሙበት የማሽላ አገዳ (ጥንቅሽ) ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችልም ነው ተብሏል።

ለአካባቢው ነዋሪዎች የስራ እድል ለመፍጠርና በግለሰብ ደረጃ የጥንቅሽ ወለላ ጭማቂ ለማምረት የመጭመቂያ ማሽኑ ንድፍ (ዲዛይን) መሰራቱንና በኢትዮጵዩ እንዲመረት ለማድረግ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸው የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር ካሳሁን ተስፋየ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራችበት ካለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ቀጥሎ የባዮ ኢኮኖሚን ማስፋፋት ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የጣፋጭ ማሽላ አገዳ ጭማቂ ለምግብነት፣ ለመድሃኒት መቀመሚያነት እና ለኢታኖል ምርት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግም በምርምር ማዕከሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የመጭመቂያ ማሽኖቹ ተሰርተው ወደ ምርት ሲገባ ለበርካቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል ።

You might also like
Comments
Loading...