Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እየሰራች ነው- አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ተግታ እየሰራች እንደምትገኝ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ገለፁ።

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የሚመራ የኢትዮጵያ ፓርላማ ልዕካን ቡድን ጥቅምት 4 እና 5 2012 ዓ.ም በቤልጄም ብራሰልስ በተካሄደው የአፍሪካ ካርቢያን፣ ፓስፊክ እና የአውሮፓ ህብርት ፓርላማ ጥምር ጉባኤ ላይ ተሳትፏል።

በጉባዔው ላይም አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ዙሪያ ገለፃ ማድረጋቸውን የህዝብ ተወካች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የልማት ትብብርንና ውህደትን ለማምጣት ያደረገውን ጥረትና በተለይም ለሱዳን እና ደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ስኬት ያበረከተው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ አክለውም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ለጉባዔው ተሳታፊዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፥ የግድቡ የግንባታ አላማም የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር እየሰራች መሆኑን እና በዚህም ሀገራቱን በመንገድ፣ በባቡርና በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተጠቃሚነት ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረት ተግታ እየሰራች እንደምትገኝም ነው የተናገሩት።

በጉባዔው የአፍሪካ ካርቢያን፣ ፓስፊክ እና የአውሮፓ ህብርት ፓርላማ ጥምር ጉባኤ ተባባሪ ፕሬዚዳንትና የአውሮፓ ፓርላማ አባላት እንዲሁም የአፍሪካ ካርቢያን፣ ፓስፊክ ቡድን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደሳለዎ መልእክት አስተላልፈውላቸዋል።

በተጨማሪም ጉባኤው በሰብሳቢዎቹ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ህዝብና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት የያዘ መግለጫ አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.