Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና የጋራ ልማት እንዲኖር የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና የጋራ ልማት እንዲኖር ስታደርግ የነበረውን ጥረት አጠናራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት ፖሊሲ ላይ የሚመክር የውይይትመድረክ በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ የኢጋድ አባል ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደርጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ እና የፖሊሲ አቅጣጫ ለታዳሚዎች አብራርተዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የጋራ ልማትን ለማጠናከር ስታከናውነው የነበረውን ስራ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን አንስተዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አለም ላይ ካሉ ውስብስብ ቦታዎች አንዱ መሆኑንሚኒስትር ዴኤታው ፥ ስደተኞች፣ የውስጥ ተፈናቃዮች፣ የአካባቢ መራቆት፣ ሽብርተኝነት እና የኢነርጂ ደህንነት ጉዳዮች እስካሁን የቀጠናው መገለጫ መሀፐናቸውን ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ በቀጠናው በአሁኑ ወቅት ከዚህ ቀደም ያልተለመደ አይነት አዎንታዊ ለውጥ እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወቅቱን በመረዳት በቀጠናው የተጋረጡ ጂኦፖለቲካዊ ፈተናዎችን ለመወጣት ተቋማዊ ሪፎርም፣ አቅም ግንባታና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ እየተዘጋጀ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲም የጎረቤት ሀገራትን ብሎም ቀጠናውን በጋራ ለማልማት የሚያስችሉ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አልማዝ መኮንን በበኩላቸው፥ በሀገራችን ያለውን ልማት ለማሳደግ ሰላምን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

ስለሆነም የሀገር ውስጥን ሰላም እንዲሁም የአካባቢውን መረጋጋት በቀጣይነት ለማስጠበቅ ከቀጠናው ሀገራት ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የውይይት መድረክ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከአሁናዊው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ፈተናዎች እና መልካም አጋጣሚዎች ዙሪያ ምክክር ይደረጋል።

በለይኩን አለም

You might also like
Comments
Loading...