Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ ባለፈው አመት ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማጓጓዙን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2011 ዓ.ም ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ደንበኞች እንዳጓጓዘ አስታወቀ፡፡

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸው አየር መንገዱ ባለፈው ዓመት ከባድ ፈተናዎች ቢገጥሙትም በስኬት ማጠናቀቁን ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡

የተለያዩ መሰናከሎች ያሳለፈው አየር መንገዱ የደንበኞች ቁጥር ሳይቀንስ መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡

የቦይንግ ኩባንያ በምርቶቹ ላይ ያለውን ችግር ማመኑ እና የካሳ ክፍያም ለመፈፀም መንቀሳቀሱ በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር መንገዱን እውቅና እና ተቀባይነቱ ከፍ እንዲል እንዳስቻለው አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም አብራርተዋል።

ሆኖም በአለም አቀፍ የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር በተወሰነ መልኩ ትርፋማነቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

አየር መንገዱ በ2012 በርካታ የአየር መንገዱን ክብርና ዝና፣ ተወዳዳሪነት እና ተመራጭ ለመሆን የሚያስችሉትን ስራዎች እንደሚያከናውን ተነግሯል፡፡

በዚህም በተያዘው ዓመት በርካታ ደንበኞቹን ለማጓጓዝ ከ20 በላይ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን እንደሚገዛ ተነግሯል፡፡

ዋና ስራ አስፈፃሚው አዳዲስ የኤርፖርቶች ግንባታ በደብረ ማርቆስ ፣ መቱ ፣ ቦረና፣ ያቤሎ እና ሚዛን አማን እንደሚከናወንም ገልፀዋል፡፡

ግንባታቸው የተጀመሩ ኤርፖርቶችን እና ተርሚናሎችን በአግባቡ እና በጥራት ከማጠናቀቅ ባሻገር የአውሮፕላን ማቆሚያዎችን ማስፋፋት እና መገንባት እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም አየር መንገዱ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ መዳረሻዎችን እንደሚያስፋፉም አስታውቋል።

በተለይም በደቡብ አሜሪካ ሀገራት በካርጎ ዘርፍ በስፋተ ለመስራት እየተንቀሰቀሰ ነው ብለዋል፡፡

የአዳዲስ ኤርፖርቶችን ግንባታ ጨምሮ በዘንድሮው አመት ለሚያከናውናቸው ተግባራቶቹ ከ5 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ የሚያደርግ መሆኑን ከአየር መንገዱ ያገኘነዉ መረጃ ያሳያል።

በመሀመድ አሊ

You might also like
Comments
Loading...