Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደሮች የትግራይ ክልልን የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲያስተዋውቁ ዶ/ር ደብረጽዮን ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ያለውን የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ እንዲሳተፉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልጥሪ አቀረቡ።

አምባሳደሮቹ ላለፉት ሁለት ቀናት በክልሉ ሲያካሔዱት በቆዩት ጉብኝት ማጠቃለያ ውይይት ላይ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ እንደገለጹት፥ የትግራይ ክልል ከመካ ቀጥሎ በእስልምና ተከታዮች ዘንድ ታሪካዊና ጥንታዊ የሆነውን አልነጃሺ መስጊድን ጨምሮ የተለያዩ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ባለቤት ነው።

“በተጨማሪም የተለያዩ ድንቅና ጥንታውያን አብያተ ክርስትያናት፣ የተለያዩ አስተሳሰቦችና እምነቶች ያሏቸው ህዝቦች አንድ ላይ የሚገኝበት ክልል ነው” ብለዋል ዶክተር ደብረጽዮን።

“አምባሳደሮቹ ለባለሃብቶቻቸው በማስተዋወቅና ሃብታቸውን እንዲያፈሱ በማነሳሳት ሊያግዙ ይገባል” ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን “የእኛ ፍላጎት ከልማት አጋር ወድሞቻችን ጋር በመሆን አብረን ሰርተን አብረን የማደግ ነው” ብለዋል።

የትግራይ ክልል የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጅነር አበበ ግርማይ በበኩላቸው፥ በክልሉ ላሉ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ምቹ ሁኔታዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

ክልሉ ለተለያዩ የመውጫና መግቢያ ወደቦች ቅርብ በመሆኑና የተለያዩ የትራንስፖርት አማራጮችም ስላሉት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ወርቅና ሳፋሪን ጨምሮ በርካታ ውድ ማእድናት፣ የእንስሳት ሃብት፣ ሁለት ትላልቅ የኢንዱስትሪ ፓርኮችና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችም ያሉበት መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉን ከጎበኙ የስድስት የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች መካከል በኢትዮጵያ የካዛኪስታን አምባሳደር ሚስተር ቢ.ሳዲኮቭ በጉብኝታቸው መደነቃቸውንና ክልሉ የበርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ ጥንታዊና ታሪካዊው አልነጃሽ መስጊድን መጎብኘታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው የተናገሩት አምባሳደሩ፥ ባለሃብቶቻቸው ወደ ክልሉ መጥተው መዋእለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

“በአዲስ አበባና በአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አምስት ትላልቅ የሀገሬ ኩባንያዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው ይገኛሉ” ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የኢንዶዠያ አምባሳደር አል ቡስራ ባስኑርን/Al Busyra Basnurn/ ናቸው።

በቀጣይ ሌሎች የሃገራቸው ባለሃብቶችም ትግራይ ክልል ውስጥ ሃብታቸውን እንዲያፈሱ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸው የየሃገሮቻቸው ባለሃብቶች ከኢትዮጵያ ብሎም ከክልሉ ጋር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መፍጠር ለላቀ ብልጽግና አስፈላጊ እንደሆነም አስረድተዋል።

 

ምንጭ፦ኢዜአ

You might also like
Comments
Loading...