Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያን ጥቅም ባስከበረና የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ እየተከናወነ ነው-ጠ/ሚ አብይ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ማንም ኃይል ኢትዮጵያን ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ሊያስቆም እንደማይችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።
 
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት አካሂዷል።
 
በጉባዔው ላይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል።
 
ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ በተለይም ግብፅ አሁን እያንፀባረቀች ካለው አቋም ጋር ተያይዞ ለቀረበው ጥያቄም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም፥ ኢትዮጵያ ክብሯን እና ጥቅሟ በሚያስጠብቅ እንዲሁም የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት በማይጎዳ መልኩ የህዳሴ ግድን ግንባታን እያካሄድች ነው ብለዋል።
 
የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ከህዳሴ ግድን ግንባታ ጋር በተያያዘ የሱዳን እና ግብፅን ህዝቦች እንዲሁም መንግስታት የመጉዳት ፍላጎት የለውም ሲሉም ተናግረዋል።
 
ይህ አጀንዳ አሁን ላይ የተነሳው ግድቡን በተያዘላት ጊዜ ባለማጠናቀቃችን ነው፤ ግንባታው ሲጠናቀቅ ልክ ጊቤ ሶስትን ጨምሮ በሌሎች የሀይል ማመንጫዎች ላይ ሲነሱ እንደነበሩ ቅራኔዎች የህዳሴ ግድብ ጉዳይም መቆሙ አይቀርምብ ብለዋል።
 
የምክር ቤቱ አባላትም ትልቁ ትኩረታቸው ግድቡ በጊዜው መጠናቀቁ ላይ መሆን እንደሚገባው እና ይህንንም በአካል ሄደው በመከታተል ጭምር ሊሆን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
 
ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል የተለየ አጀንዳ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ከዚህ ቀደም ውይይቶች መደረጋቸውን እና በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥም ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ ኤልሲሲ ጋር ተገናኝተው ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸውንም አስታውቀዋል።
 
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የምትገነባው የራሷን ጥቅም ለማግኘት እንጂ የማንንም ጥቅም ለመጉዳት አይደለም፤ ስለዚህ ሌሎችም ይህንን ቢደግፉ መልካም ነው ብለዋል።
 
በተለይም የግብፅ መንግስት እና ህዝብ ቢችሉ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ልማት በቀጥታ ቢደግፉ ጥቅሙ ለነሱ ነው ያሉ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ደኗን ካበዛች ውሃ ይበዛል፤ እዚህ ላይ ማተኮርም ተበጊ ነው ብለዋል።
 
ከዚህ ውጪ ግን እርምጃ ይወሰዳል በሚል ለሚሰማው ነገር ውጊያ መፍትሄ አይሆንም፤ አስፈላጊ ከሆነ ግን ሁሉም ባለው አቅም ሊሰማራ ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ ማንም ሀይል ኢትዮጵያን ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ሊያስቆማት እንደማይችል ህዝቡ እንዲገነዘብ አሳስበዋል፡፡
 
መንግስት ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ምርጥ ምርጥ ፕሮጀክቶችን ያስቀጥላል፤ መንግስት ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ስህተቶችን ያርማል እንጂ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን አያቋርጥም፤ ምክንያቱም ፕሮጀክት እያቋረጡ ሀገር መገንባት ስለማይቻል ብለዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሀገር ውስጥ ሰላም ጉዳይ ይልቅ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ ይሰጣል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ ባላት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት ከሌሎች ሀገራት በተለየ ሁኔታ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የምትሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።
 
ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር የተለያዩ ግንኙነቶችን ለመፍጠር የባህር በር ካላቸው ሀገራት ጋር አስተማማኝ ግንኙነት መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አንስተዋል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በዘር፣ በሃይማኖት፣ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ጥብቅ ትስስር ያላት በመሆኑ፥ከእነዚህ ሀገራት ጋር ያላትን ዘላቂ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በስፋት ይሰራል ነው ያሉት።
 
በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን መሰረት ከአሜሪካ እና ቻይና ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጅቡቲ፣ኤርትራና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ጋር ባለን ግንኙነት ዙሪያ በቅርበትና በቅድሚያ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል።
 
ይህ ማለት ግን መንግስት ለሀገር ውስጥ ሰላም ጉዳይ ትኩረት ካለመስጠት የመጣ አለመሆኑን አብራርተዋል ።
 
የሀገር ውስጥ ሰላምን ከማስከበር አንፃር መንግስት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶች በዘላቂነት ለማስወገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቦታው ድረስ በመሄድ ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡
 
በችግሩ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አክለዋል።
 
የሀገር ውስጥ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት እና በእስልምና እምነት ተከታዮች ውስጥ የነበሩ ልዩነቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት መቻሉን ተናግረዋል ፡፡
 
ከዚህ ባለፈም በሀገር ውስጥ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው እስር ላይ የነበሩ ዜጎችን ከማስፈታት ባሻገር በውጭ ሀገራት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ እስር ቤት የነበሩ ዜጎችን በማስፋት በሰላም ሀገራቸው እንዲገቡ ተደርጓል ነው ያሉት ጠቀላይ ሚኒስትሩ፡፡
 
ስለሆነም ኢትዮጵያ ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንፃር ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የምትሰጥ ቢሆንም የሀገር ውስጥ ሰላምን ማስከበር ግን ከሁሉም የሚቀድም መሆኑን ነው ያነሱት፡፡
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዋጋ ንረትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሀገር ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ችግር በአቅርቦት ችግር ሳይሆን በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የሚፈጠር መሆኑን ተናግረዋል።
 
የቤት አቅርቦት ችግር፣ ሰፊ የስራ ዕድል አለመኖር እና የምርት ገበያው በሚፈለገው መልኩ ለተጠቃሚዎች አለመድረስም ለዋጋ ንረቱ መባባስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ መሆኑን ጠቁመዋል ።
 
የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያማከለ የቤቶች ግንባት የሚከናወን መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በሁለት ወራት ውስጥ በጎተራ አካባቢ ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ዘመናዊ መንደር የሚገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
 
የጎዳና ተዳዳሪዎችን በዘላቂነት ለማንሳት በተጀመረው ዕቅድ መሰረትም በቅርቡ ከ4 ሺህ እስከ 5 ሺህ ለሚደርሱ ቤት አልባ ዜጎች ቤት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።
 
የምግብ የዋጋ ንረትን ለመቅረፍም በመዲናዋ በሁለት ወራት ውስጥ በቀን አንድ ሚሊየን ዳቦ የሚያመርተው ፋብሪካ ተጠናቆ ስራ የሚጀመር መሆኑን ተናግረዋል።
 
በተጨማሪም ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በተገኘ ድጋፍ በቀን 10 ሚሊየን ዳቦ ማምረት የሚችል ፋብሪካ የሚገነባ መሆኑን ነው የገለጹት ።
 
በሌላ በኩል በተያዘው በጀት ዓመት ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የመኖ አቅርቦትን በተሻለ መልኩ ለማዳረስ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
ከእንስሳት ሃብት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም በቁም ወደ ውጭ የሚላከበትን ሂደት በመቀነስ በሀገር ውስጥ የእንስሳት ተዋፅኦዎችን በማቀነባበር መላክ እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መስህቦች መገኛ መሆኗን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፥ ዘርፉ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ ለሀገራችን ጥሩ ገቢ እንዲያስገኝም ሁሉም ማህበረሰብ የበኩልን ድረሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።
 
ዘርፉን ለቱሪስቶች ይብልጥ ተደራሽ ለማድረግም የመሰረት ልማት ዝርጋታ፣ የሆቴልና ምግብ አቅርቦት፣የመስተንግዶ ሁኔታ እና ሌሎች አቅርቦቶችን ማዘመን እንደሚያስፍልግ ጠቁመዋል።
 
ይህም ከተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች ማራኪ ጊዜ እንዲኖራቸው ከማድረጉ ባለፈ ኢትዮጵያን ከማስተዋወቅ አንፅር ጉልህ መና የሚጫወት መሆኑን ተናግረዋል።
You might also like
Comments
Loading...