Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቦንጋ ከነዋሪዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ቦንጋ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ተወያዩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአዳራሽ ውይይቱ በፊት በከተማዋ ስታዲየም ለተሰበሰበው የከተማዋ ነዋሪዎች ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸው የካፋ ህዝብ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውን ከተፈጥሮ ጋር ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር፣ ራስን የማስተዳደር:፣ የተቋማት ግንባታ፣ የሥራ ክፍፍል ከፍተኛ ልምምድ እንዳለው አስታውሰዋል።

በመሆኑም በውይይትና በምክክር ሀገር ማልማትን ለሌሎችም ለማካፈል መነሳት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አዲሱ ዓመት 2012 የፍቅር፣ የሰላም፣ የደስታና የመደመር እንዲሆንም ተመኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዞኑ እና ከሀገር ሽማግሌዎች የፈረስ፣ ጋሻና ጦር ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እና የኢፌዴሪ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ ተገኝተዋል።

በውይይቱ ነዋሪዎቹ በክልል ከመደራጀት፣ ከመሰረተ ልማት እና ከጤና ተቋም ግንባታ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፥ ዞኑ ካለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን ኢንቨስትመንት እንዲመጣም ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በቦንጋ ከተማ ከአመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው ብሔራዊ የቡና ሙዚየምና የቦንጋ ከተማ የውሃ ፕሮጀክት መጓተትንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በምላሻቸው ጥያቄዎችን በምክክር አቅም በፈቀደ መጠን ለመመለስ ቃል ገብተዋል።

አቅም ያላቸው አልሚ ባለሀብቶች እንዲመጡ መሥራትና በመተባበርና በስልጣኔ የመንቀሳቀስን አስፈላጊነት በማንሳት ተፈጥሮንና አከባቢን ለመንከባከብ ያሳዩትን ቆራጥነትም አድንቀዋል።

የክልል አደረጃጀት ለውጥ የሁሉም ጥያቄ መልስ አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ተያያዥነት ያላቸው አማራጭ አሰራሮች ማየት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

በመጨረሻም በትብብርና በመደመር በመሥራት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

 

በአልአዛር ታደለ

You might also like
Comments
Loading...