Fana: At a Speed of Life!

የፓለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ያቀረቡበት የምርጫና የፓለቲካ ፓርቲዎች ህግ አስፈላጊው ውይይት ተካሂዶበታል- ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፓለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ያቀረቡበት የምርጫና የፓለቲካ ፓርቲዎች ህግ አስፈላጊው ውይይት እንደተካሄደበት ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ቡርቱካን ሜዴቅሳ ጉዳዩን አስመልክተው በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በቅርቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ያቀረቡበት የምርጫና የፓለቲካ ፓርቲዎች ህግ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በሀገሪቱ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ፓርቲዎች በተገኙበት ሶስት ጊዜ አስፈላጊው ውይይት የተካሄደበት መሆኑን ገልፀዋል።

ፓርቲዎች ህጉን አናውቀውም አልተሳተፍንበትም በማለት ያነሱት ቅሬታ ተገቢ አይደለም ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን፥ምን አልባት በቂ ውይይት አልተደረገም የሚል ቅሬታ ሊነሳ ይችላል ብለዋል።

ወይዘሪት ብርቱካን በሀገሪቱ ከሚገኙ ፓርቲዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በምርጫ ቦርድ እውቅና ባይሰጣቸውም በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ እና ከእስር ቤት የወጡ በመሆናቸው በሚዘጋጁ መድረኮች እንዲሳተፉ ተደርጓል ነው ያሉት።

በመግለጫቸው በርካታ ጉዳዮችን ያነሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ቡርቱካን፡- የቦርድ አመራረጥ፣ በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ጫና ሳይደረግበት ገለልተኛ ሆነ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የህዝብ ቆጠራ ሳይካሄድ ሀገራዊ ምርጫ መካሄዱን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

በምላሻቸውም በምርጫ ውጤት ላይ ለውጥ የሚያመጣው አሁን ያለው የህዝብ ቁጥር መረጃ ሳይሆን በምርጫው ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር መሆኑን ገልፀዋል።

ሆኖም የህዝብ ቁጥር መረጃን፣ የምርጫ ጣቢያዎችን ለማዘጋጀት እና የምርጫ አስፈፃሚዎችን ለማስተካከል ከስታቲስቲክስ ከሌሎች ተቋማት መረጃዎችን እንደሚሰበሰቡ ተናግረዋል።

የምርጫ ምዝገባ ሂደቱም ለጋዜጠኞች እና ፓርቲዎች ክፍት እንደሚሆን የጠቆሙ ሲሆን፥ፓርቲዎች በዚህ ቅሬታ ካላቸውም ማቅረብ ይችላሉ ብለዋል።

በሌላ በኩል የሲዳማ ዞንን ህዝበ ውሳኔ በተመለከተ አስፈላጊውን በጀት የሚሸፍነው የክልሉ መንግስት ወይንም ምክር ቤት እንደሆነ ገልፀዋል።

የህዝበ ውሳኔው ጥያቄ ከክልሉ የመጣ እና ምርጫ ቦርድ በጀት ያልያዘለት በመሆኑ በጀቱ በክልሉ መንግስት ወይንም በምክር ቤቱ ይሸፈናል ብለዋል።

የህዝበ ውሳኔው ጥያቄ ከክልሉ የመጣ እና ምርጫ ቦርድ በጀት ያልያዘለት በመሆኑ በጀቱ በክልሉ መንግስት ወይንም በምክር ቤቱ ይሸፈናል ብለዋል።

ከሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሀዋሳ ከተማን ጨምሮ የሀብት ክፍፍልን በተመለከተ የህግና አስተዳደር ጉዳዮች ከመስከረም 22 ቀን 2012 በፊት እንዲቀርብ ስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ ለሚካሄደው ምርጫ 250 ሺህ የምርጫ አስፈፃሚዎች እንደሚመለመሉ የሚጠበቅ ሲሆን ይህንን ገለልተኛ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህ ቀደም በታችኛው እርከን የምርጫ ቦርድ ስራን በተለይ ቀበሌዎች እና ወረዳዎች ሲሰሩ እንደነበረ እና ይህም ገለልተኝነቱ ላይ ጥያቄ ሲያስነሳ እንደነበረ ገልፀዋል።

አሁን ግን ይህን ጉዳይ እንዲቀር መወሰኑን ወይዘሪት ብርቱካን አስታውቀዋል።

ከነገ ማለትም ነሃሴ 30 ቀን 2011 ጀምሮ የሲዳማን ህዝበ ውሳኔ አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መካሄድ ይጀምራል ተብሏል፡፡

መስከረም 7 ደግሞ ህዝበ ውሳኔው ከመካሄድ በፊት እና ከተካሄደ በኋላ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ይካሄዳል፡፡

በኤፍሬም ምትኩ

You might also like
Comments
Loading...