Fana: At a Speed of Life!

የወባ በሽታን እስከ ፈረንጆቹ 2050 ድረስ ማጥፋት እንደሚቻል አንድ ሪፖርት አመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 4 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የወባ በሽታን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2050 ድረስ ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት እንደሚቻል የባለሙያዎች ሪፖርት አመላከተ።

የባለሙያዎቹ ሪፖርት የወባ በሽታ በአንድ የትውልድ ጊዜ ውስጥ ከምድራችን ሊጠፋ እንደሚችል አመላክቷል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያችን እና ተመራማሪዎችን ባካተተው ቡድን ይፋ የሆነው ሪፖርት ገዳዩን የወባ በሽታ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ማጥፋት እንደሚቻል ያትታል።

ይህን እውን ለማድረግ ግን አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን እና መከላከያ ዘዴዎችን በአግባቡ መተግበርና ጥቅም ላይ ማዋል ይገባልም ነው ያሉት ባለሙያዎቹ።

የወባ በሽታን ማጥፋት ከባድ እንደማይሆን ያነሳው የባለሙያዎች ሪፖርት፥ በሽታ አምጭውን ጥገኛ ተዋህስያን ለማስወገድ ግን በየዓመቱ 2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልጋልም ነው ያለው።

ዓለም ላይ በየዓመቱ ከ200 ሚሊየን በላይ ሰዎች በወባ ሲጠቁ፥ በአብዛኛው ህጻናት የሆኑ 435 ሺህ ሰዎች ደግሞ ለህልፈት እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያመላክታሉ።

የወባ በሽታን ለመከላከል በየዓመቱ ወደ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደሚደረግም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

የወባ በሽታ አምጭ ትንኝ ንክሻን ለመከላከል በተሰራው ስራና የተሻሻሉ መድሃኒቶችን ማቅረብ መቻሉን ተከትሎ ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ ወባን በመቆጣጠር ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

በዚህም የወባ በሽታ ያለባቸውን ሃገራት ቁጥር ከ106 ወደ 86 ማውረድ ተችሏል ነው የተባለው።

ከዚህ ባለፈም በወባ የመያዝ መጠን በ36 በመቶ ሲቀንስ የሞት መጠን ደግሞ በ60 በመቶ ቀንሷል ነው የተባለው።

ዓለም ላይ ካለው የወባ ወረርሽኝ ውስጥ ግማሹ የአምስት የአፍሪካ ሃገራት ድርሻ መሆኑን፥ ከተመራማሪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶክተር ዊኒ ፓንጁ ሹምቡሾ ተናግረዋል።

ከሶስት አመት በፊት በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ተልዕኮ የተሰጠውና በ41 ባለሙያዎች የተጠናከረው ሪፖርት በዓይነቱ የመጀመሪያ ነው ተብሏል።

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like
Comments
Loading...