Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ፎረሙ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ሲሆን፥ በቆይታውም በዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ፣ በአፍሪካ ያሉ ሆቴሎች አቅም እና አፍሪካን የቱሪዝም እና የጉዞ መዳረሻ ለማድረግ ምን መሰራት አለባቸው በሚለው ላይ ይመክራል ተብሏል።

በዛሬው እለት በተካሄደው የፎረሙ መክፈቻ ላይም የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ ከ52 ሀገራት የተውጣጡ የሆቴል ዘርፍ ባለሙያዎች ተካፍለዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ለፎረሙ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ አፍሪካ በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ ብዙ ያልተሰሩ ስራዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን ተሞክሮ ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪዝም ሀብት ያላት ሀገር ቢሆንም፤ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባትን ያክል እንዳልተጠቀመች አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀም የሆቴል ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ሚና እንዳለው በመግለጽ፤ መንግስት በሆቴል ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የቫን ማርከን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ኒክ ቫን ማርከን፣ የራዲሰን ሆቴል ግሩፕ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ቲም ኮርደን፣ የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል የህንድ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጉዋቪን ፓስካል እንዲሁም የአኮር ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዊልስ በአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በምን መልኩ በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ በስፋት መሰማራት ይቻላል የሚለው ላይም ሀሳብ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

You might also like
Comments
Loading...