Fana: At a Speed of Life!

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ እንደሚከበር ተገለፀ።

14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም አስታውቀዋል።

በበዓሉ ዝግጅት ዙሪያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች በተገኙበት ውይይት እየተደረገ ነው።

በውይይቱ ላይም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም፥ እስካሁን በተከበሩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጥቅሞች እና ጉድለቶች ዙሪያ ጥናት መደረጉን ገልፀዋል።

በጥናቱ የተለዩ መልካም ጎኖችን በማጠናከር በዘንድሮውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የዘንድሮው 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህገ መንግስታዊ መከበር እና ሀገራዊ አንድነትን ታሳቢ አድርጎ እንደሚከበርም ተናግረዋል።

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በውይይት መድረኩ ላይ፥ የኦሮሚያ ክልል ህዳር 29 2012 ዓ.ም በሚከበረው 14ኛው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በለይኩን አለም

You might also like
Comments
Loading...