Fana: At a Speed of Life!

የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር አተረፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2011 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሮባ መገርሳ የ2011 እቅድ አፈጻጸምና የ2012 በጀት አመት እቅድን ይፋ አድርገዋል።

በመግለጫቸው ድርጅቱ ባለፈው ዓመት 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን መጠን ያለው ዕቃ ማጓጓዙን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ ውስጥም 2 ሚሊዮን ቶን ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ ማዳበሪያና ስንዴ ናቸው ብለዋል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በጅቡቲ በመገንባት ላይ የሚገኘው የ120 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ መጓተት፣ በደረቅ ወደቦች የሚከሰት የኮንቴነሮች ክምችት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር የቅንጅት ውስንነት፣ የአስተዳደርና የቴክኖሎጂ ክፍተቶች ድርጅቱ ባሳለፈው በጀት አመት አገልግሎቱን ቀልጣፋ እንዳያደርግ ማነቆ የሆኑበት ጉዳዮች መሆናቸውን ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሮባ ገልፀዋል።

ድርጅቱ በ2010 ከነበረው አፈጻጸም በ2011 በዋጋ፣ በቅልጥፍና እና በአገልግሎት አሰጣጡ በደንበኞች ተመራጭ መሆኑን እና ይህንኑ በ2012 በጀት ዓመትም ለማስቀጠል የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍ እየሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

በ2011 በጀት አመት የጭነት አገልግሎት ሲሰጥ የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በ2012 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን የጭነት አገልግሎት ለመስጠት ማቀዱ ተመልክቷል።

 

በቆንጂት ዘውዴ

 

 

You might also like
Comments
Loading...