Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥልቅ ማሻሻያ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 30፣2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሆኑት የኢትዮጵያ ልማት ባንክና የኢትዮጵ ንግድ ባንክ ጥልቅ ማሻሻያ እያደረጉ ነው።

የሚደረገው ማሻሻያ መንግስት በቀጣይ 3 ዓመታት የሚተገብረው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ አዋጭ ስለመሆኑና ባንኮችም በየዓመቱ በመቶ ሚሊየኖች ከዚህ ባለፈም በቢሊየኖች የሚቆጠር ትርፍ ማትረፋቸው ይነገራል።

የባንኮች የውጤታማነትና የትርፋማነት ሁኔታ ግን ወደ መንግስታዊ የፖሊሲ ባንክ የሚባሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ሲመጣ የተለየ ገጽታን ይይዛል።

ለምሳሌ ግዙፉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጠናቀቀው የ2011 በጀት ዓመት 17 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ማትረፉን አስታውቋል።

በሌላ በኩል ባንኩ በ100 ቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብን ለመንግስት የልማት ድርጅቶች አበድሮ እንዳልተመለሰለት ይነገራል ።

በገንዘብ ሚኒስቴር በየዓመቱ የሚታተመው የመንግስት ዘርፍ የብድር ክምችት ሰነድና ሌሎች ሪፖርቶች የንግድ ባንክ ለመንግስት የልማት ደርጅቶች ከ400 ቢሊየን ብር በላይ ብድር መስጠቱን ይገልጻሉ ።

ይህን ያክል መጠን ያለው ብድር መመለስ ያለበት ጊዜ አልፎ አለመመለሱም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ይህ ሁኔታም አጠራጣሪ ከሆነ ብድር አንጻር ባለ መለኪያ ንግድ ባንኩ ያለበትን ጤናማነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ብድሩን የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች ሲያልቁ እንደሚመልሱ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል፣የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን የመሳሰሉ የልማት ድርጅቶች ናቸው የንግድ ባንክን ያልተመለሱ ብድሮችን የያዙት።

ከእነዚህ የልማት ድርጅቶች ውስጥ ብድሩ ይሰረዝልን ያሉ እንደነበሩም ተሰምቷል

የኢትዮጵያ ልማት ባንክም ኪሳራ ያጋጠመውና ከሰጠው ብድር ያልተመለሰለት ከተቀመጠው የ15 በመቶ ምጣኔ በላይ ነው ።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ባንኩ እስካሁን ካበደረው 46 ቢሊየን ብር 40 በመቶ የሚደርሰው ወይም 18 ቢሊየኑ መመለሱ አጠራጣሪ ሆኗል።

በዚህ ምክንያትም የባንኩ ካፒታል ተሟጦ መንግስት ተጨማሪ ካፒታል እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል።

ቁጥሮቹ እንደሚያመላክቱት ንግድ ባንክም ሆነ ልማት ባንክ ጤናማነታቸው ከሚለካባቸው ያልተመለሰ ብድር መለኪያ አንጻር ክፍተት እንዳለባቸው የሚታይባቸው ናቸው።

ከዚህ እና ሌሎች መነሻዎችም ሁለቱ ባንኮች ጥልቅ ማሻሻያ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስተር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ተናግረዋል።

መንግስት ከገባበት የብድር ጫና ውስጥ ግማሹ ከሀገር ውስጥ የተወሰደ ሲሆን፥ከዚህ ውስጥ ብዙውን የየያዘው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላለፉት ዓመታት ለልማት ድርጅቶች ሰጥቶ በፕሮጀክቶች ውጤታማ አለመሆን ሳቢያ ያልተመለሰ ነው።

በዚህ ምክንያት ወደ ገበያው የገባ ገንዘብ ደግሞ የልማት ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸውም ግሽበትን በማምጣት ለጥቅል ኢኮኖሚው ችግር በመፍጠር አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ባንኮቹ ማሻሻያ የሚያደርጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ የፖሊሲ ባንኮች ላይ የሚደረገው ማሻሻያ ኢትዮጵያ በቀጣይ ሶስት ዓመታት የሚተገበረው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አካል መሆኑንም አክለዋል።

ከዚህ አንጻር ባንኮቹ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ከሌሎች የግል ንግድ ባንኮች ጋር በእኩል የሚታዩበት ሁኔታ ይፈጠራል ነው የተባለው።

በተለይ የግል ባንኮች መንግስት የፖሊሲ ባንኮቹን የሚረዳበት መንገድ እኛን ከውድድር አስወጥቶናል በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማሉ።

መንግስት የውጭ ምንዛሬን ለፖሊሲ ባንኩ በሚሰጥበት ጊዜ ደንበኞች ለዚህ ምንዛሬ ሲሉ የግል ባንኮች ጋር ያስቀመጡትን ገንዘብ ያወጣሉ፤ለዘርፎች የሚሰጥ ብድር ላይም ልዩነት ይደረግብናል ሲሉ ይደመጣሉ።

ከዚህ አንጻር አሁን የተወሰኑ ማሻሻያዎች ቢታዩም የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ባለፈው ሳመንት የሶሰት ዓመቱን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሲያቀርቡ ሁለቱ ባንኮች በኢንዱስትሪው መርህ ብቻ እንዲሄዱ ይደረጋል ብለዋል።

ሌላኛው የፖሊሲ ባንክ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚያበድረውን ገንዘብ በብዛት የሚያገኘው የግል ባንኮች ከሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ በብሄራዊ ባንክ በኩል ቦንድ እንዲገዙ በማድረግ ነው።

ልማት ባንኩ በዚህ መልኩ ያገኘውን በ10 ቢሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማበደሩ ምክንያት ውጤታማነቱ ቸግር ውስጥ የገባ መሆኑ ተነግሯል።

አሁን እነዚህ ባንኮች በገበያው ተወዳዳሪነታቸው እንዲዳብር ሲፈለግም መንግስት በጊዜ ሂደት የ27 በመቶ ቦንድ ስርዓቱን የሚተው ይሆናል ብለዋል ዶክተር እዮብ ።

እነዚህን የፖሊሲ ባንኮች ከከፍተኛ ያልተመለሰ ብድራቸው ነጻ ማድረግም ለወደፊት ለማክሮ ኢኮኖሚው የሚሰጠው ጠቀሜታ መኖሩም ተመላክቷል።

ለዚህ የሚደረገው ማሻሻያም የአወቃቀርና ሌሎች ስራዎቸን ሊያካትት የሚችል መሆኑ ነው የተገለጸው።

የብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴም ባንኮቹ የሚያደጉት ማሻሻያ ከዚህ ችግር ያወጣቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በካሳዬ ወልዴ

You might also like
Comments
Loading...