Fana: At a Speed of Life!

አዲሱ አመት ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር በስኬት የምንራመድበት ሊሆን ይገባል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 6 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ አመት የሰላም፣ የጤና፣ የብልፅግና፣ እና ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር በስኬት የምንራመድበት ሊሆን እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቷ አዲሱን አመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም አዲሱ አመት ተስፋን በመሰነቅ ለተሻለ ህይዎት ራስን የምናዘጋጅበት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የተጠናቀቀው አመት ከችግሮች ባሻገር በሃገሪቱ በርካታ በጎ ነገሮች ይዞ የመጣ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችሉ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያና ማህበራዊ መስኮች መሰረት የጣሉ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በአመቱ የሴቶችን እኩልነት ለማረጋገጥ በሩ መከፈቱን ጠቅሰው፥ በሩ እንዳይዘጋና በርካታ ሴቶች እንዲያልፉበት ሁሉም ሊረባረብ ይገባዋልም ነው ያሉት።

በአመቱ በአመለካከታቸው ሳቢያ ተራርቀው የነበሩ ዜጎች በሃገር ጉዳይ ለመወያየት መብቃታቸውንም አንስተዋል።

በተቃራኒው የሃገሪቱን ህልውና የተፈታተኑ ግጭቶችና በሃገር ውስጥ የዜጎች መፈናቀል መከሰቱን አስታውሰው፥ መሰል ክስተቶች እንዳይደገሙ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል ብለዋል።

ወገኖችን ከድህነት ማላቀቅ፣ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን እና መብቶቻቸውን ማስከበርም ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርግና ሊያስተሳስር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአዲሱ አመትም ሃገሪቱ በፅኑ መሰረት ላይ የምትቀመጥበት፣ ተቋሞች ተቋማዊ አሰራር የሚዘረጉበትና አንድነት የሚጠናከርበት መሆን እንዳለበትም አውስተዋል።

ከዚህ ባሻገርም ደህንነቷ የተረጋገጠችን ሃገር እውን ለማድረግም ዜጎች አንድነታቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

አዲሱ አመትም ለመላው ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር እና የብልጽግና እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

 

 

በአወል አበራ

 

You might also like
Comments
Loading...