Fana: At a Speed of Life!

አቶ ባልቻ ሬባ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 9 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ባልቻ ሬባ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ቴሌኮሙዩኒኬሽን በጸደቀው አዋጅ ቁጥር 1148/2011 መሰረት፥ የቴሌኮም ዘርፉን በመቆጣጠር በዘርፉ ለሚሰማሩ የግል ተቋማት የውድድር ሜዳውን ምቹ ለማድረግ የተቋቋመ ነው።

አቶ ባልቻ ሬባም ተቋሙን ከመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተሾመዋል።

አቶ ባልቻ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፥ በኦሮሚያ ውሃ ሃብት ቢሮ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ተቆጣጣሪ በመሆን አገልግለዋል።

አቶ ባልቻ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ኤጀንሲ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ከዋና ክፍል ኃላፊ እስከ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል።

ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር የስታንዳርድና ቁጥጥር ዳይሬክተር ሆነው ማገለግላቸውም ታውቋል።

ላለፈው አንድ ዓመት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴሌኮም፣ ፖስታ እና ኮሙዩኒኬሽን ቁጥጥር ላይ ያተኮረው የስታንዳርድና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነበሩ።

በስራው ዓለም ላለፉት 15 ዓመታት በቴሌኮም የቁጥጥር ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል።

በባሃሩ ይድነቃቸው

You might also like
Comments
Loading...