Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ ዓመት በክልሉ ለሰላምና ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተለየ ትኩረት ይሰጣል- አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል በአዲሱ ዓመት ሰላምና መረጋጋትን በማጠናከር ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱን ዓመት አስመልክተው ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፥ አዲሱ ዓመት ኃይማኖት፣ ብሄርና ቋንቋ ሳይለይ ሁሉም በአንድነት ሊያከብረው የሚገባ ልዩ በዓል ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልልም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ግጭት፣ መፈናቀልና አለመረጋጋቶች በስፋት የተስተዋሉበት እንደነበርም አስታውሰዋል።

በተለይም ያለፈው ዓመት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የነበሩና ሌሎች አመራሮችም በሞት የታጣበት በመሆኑ በቀላሉ ሊረሳ የማይችል ወቅት መሆኑን አመልክተዋል።

ካለፉት ችግሮች ትምህርት በመውሰድም በመጭው ዓመት በአዲስ ጉልበት ለሰላምና መረጋጋት የተለየና የተቀናጀ ስራ ለመስራት እቅድ ተነድፎ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

ክልሉ የቀደመ የሰላም ተምሳሌትነቱን በማምጣት ለቱሪዝምና ለሌላውም ልማት እንቅስቃሴዎች እንቅፋት የማይፈጥር የተረጋጋ አካባቢን ለመፍጠር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ለፀጥታ መዋቅሩ ብቻ የሚተው ሳይሆን ወጣቱ፣ ምሁራን፣ የኃይማኖት መሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ከመንግስት ጎን በመሆን በባለቤትነት እንዲንቀሳቀሱም አመልክተዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም ከአፍራሽ ተግባራት ተቆጥበው ስለ ሰላምና ልማት ህብረተሰቡን በማንቃትና በማስተባበር የተጠናከረ የገጽታ ግንባታ ስራዎችን ሊደግፉ ይገባልም ነው ያሉት።

የክልሉ አመራር ከመቼውም ጊዜ በላይ አቅሙን አጎልብቶና ጎልቶ የወጣበት ጊዜ ላይ የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፥ ከሌሎች እህት ክልሎች ጋር በሠላም ዙሪያ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በሌላ በኩል በአዲሱ ዓመት ለአንድ ሚሊየን ስራ ፈላጊ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ግብርና፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ለወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጠርባቸው ዘርፎች መሆናቸው ነው የተገለጸው።

በአዲሱ ዓመት ከሰላምና ልማት ስራው ባልተናነሰ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራን ከልማዳዊ አሰራር በማላቀቅ መሰረታዊ ችግር የመፍታት ስራ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

“ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራም ለግብርና እድገቱ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን በማሻሻልና በመተግበር በርካታ ወጣቶችን የሚሸከም ማዕቀፍ ሆኖ ይሰራል” ነው ያሉት በንግግራቸው።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በኢንቨስትመንት ዘርፉም የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ እንዲገቡ በማድረግ ለስራ እድል ፈጠራው የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።

በራሱ አቅም እያደገ የመጣውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ በተሻለ አሰራር በማገዝ ለስራ እድል ፈጠራው ጠቀሜታ እንዲውል በተለየ ትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

እነዚህንና ሌሎች የልማት አማራጮችን በመጠቀምም በ2012 ዓ.ም ከአንድ ሚሊየን ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን አውስተዋል።

የታቀደው የስራ እድል ፈጠራ ውጤታማ እንዲሆንም ወጣቶች የስር ፍቅርና ፍላጎት ኖሯቸው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ለክልሉ ነዋሪዎችና ለሌሎችም ኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የልማት የብልጽግና፣ የመተሳሰብ ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ምንጭ ፦ኢዜአ ፣ ተጨማሪ መረጃ ናትናኤል ጥጋቡ

You might also like
Comments
Loading...