Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ አመት በአንድነት መንፈስ በጋራ መስራት እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 6 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ አመት ራስን በማደስ በመፈቃቀርና በአንድነት መንፈስ በጋራ መስራት እንደሚገባ የሃይማኖት መሪዎች ተናገሩ።

የተለያዩ የሃይማኖት መሪዎች አዲሱን አመት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፥ በአዲሱ አመት ጎጂ እና አላስፈላጊ ድርጊቶችን ማሰናበት ይገባል ብለዋል።

ራስን አብሮ ማደስ ያስፈልጋል ያሉት ብፁዕነታቸው አዲሱን አመት ለመፈቃቀር እና ለአንድነት ልንሰራበት ይገባል ሲሉም አባታዊ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር እድሪስ በበኩላቸው፥ ህዝቡ በእያንዳንዱ ሰዓት እና ቀን የሚያከናውናቸውን ተግባራት በመፈተሽ ድክመቱን ማረም ይኖርበታል ነው ያሉት።

አዲሱ አመትም ለአንድነት የምንቆምበት እና ያለፈውን በመገምገም ቀጣይ እቅድ የምናወጣበት ሊሆን ይገባልም ብለዋል በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ደግሞ ያሳለፍነው አመት ጥሩ እና መጥፎ ጉዳዮችን ያስተናገድንበት አመት እንደነበር ጠቅሰዋል።

አዲሱን አመት መልካም እና ብሩህ ለማድረግ ውስጥን ማደስ እንደሚገባም በመልዕክታቸው አንስተዋል።

አዲሱን አመት ስንቀበልም ችግረኞችን እና ጠያቂ የሌላቸውን ወገኖች በማሰብ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዛ በአዲሱ አመት፥ መልካሙን በማጠናከር ጎጅ ተግባራትን ማስወገድ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ፈጣሪ የቸረን መልካም ሃገር ሁለንተናዊ እድገት እንድታስመዘግብ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሃይማኖት መሪዎቹ በአሮጌው አመት ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ጎጅ መሆናቸውን በመረዳት ለሃገር እና ወገን የሚያስብ ትውልድ ለመቅረጽ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመጨረሻም አዲሱ አመት የስኬትና መልካም ይሆን ዘንድም መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

በይስማው አደራው

 

You might also like
Comments
Loading...