Fana: At a Speed of Life!

በባሕር ዳር ከተማ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ተያዘ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 7 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በባህር ዳር ከተማ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መያዙን የአማራ ክልል አድማ ብተና 2ኛ ሻለቃ 1ኛ ሻምበል ምክትል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ታለማ ዳኛ አስታወቁ።

ምክትል ኢንስፔክተሩ ለአብመድ እንደተናሩት በ20 ጆንያዎች የተቋጠረ 497 ሽጉጥ እና ወደ 46 ሺህ የሚገመት ጥይት በባሕር ዳር ከተማ ተይዟል።

የጦር መሳሪያው ከብሔራዊ መረጃ ደህንነትና ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት ከነዳጅ ጋር ተቀላቅሎ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ በገባ የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴ ውስጥ ሲጓጓዝ ነው የተያዘው።

ከትናንት ምሽት ጀምሮ በተደረገ ክትትልም መሳሪያው ባሕር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ መያዙን ተናግረዋል።

አሽከርካሪው ለማምለጥ ሙከራ አድርጎ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ያስታወቁት ምክትል ኢንስፔክተር ታለማ፥ ነዳጁ ከባሕር ዳር አልፎ የሚሄድ እንደነበርና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያውን ከቦቴው ለማውጣት የሚያገለግል ብረት በተሽከርካሪው ውስጥ  መገኘቱን ገልጸዋል።

በተያያዘ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በታች አርማጭሆ ወረዳ በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 3 ሺህ 555 የብሬን ጥይት ተይዟል።

ጥይቱ የታርጋ ቁጥሩ ኮድ 3 አ.አ 84556 በሆነና ከዳንሻ ወደ ጎንደር መስመር ሲጓዝ በነበረ ተሽከርካሪ መያዙን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

ከጥይቱ በተጨማሪም በርካታ የባንክ ደብተር ከአሽከርካሪው እጅ መገኘቱ ተገልጿል።

 

You might also like
Comments
Loading...