Fana: At a Speed of Life!

በበዓል ግብይትና በዋዜማ በዓል አከባበር ኅብረተሰቡ ራሱን ከአደጋና ከወንጀል ጥቃት መጠበቅ አለበት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበዓል አከባበር ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ የእሳትና ሌሎች አደጋዎች ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ነዋሪዎቹ ከወትሮው የተለየ መጨናነቅ በሚስተዋልበት የበዓል ግብይትና የዋዜማ በዓል አከባበር ኅብረተሰቡ ራሱን ከአደጋና ከወንጀል መጠበቅ አለበት ብለዋል።

ለበዓል የሚዘጋጁ ምግቦች በሚሰናዱበት ወቅት ከከሰል ጭስና ኤሌክትሪክ አጠቃቀም ጉድለት የተነሳ የሚስተዋሉ ችግሮች ይኖራሉ።

እንዲሁም በዓሉ በሚከበርበት እለት ጠጥቶ ከማሽከርከርና በፍጥነት ከማሽከርከር ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ የትራፊክ አደጋዎች እንዲሁም መጨናነቅና ግርግርን ተከትለው የሚኖሩ የስርቆትና ተያያዠ ወንጀሎችም አሉ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከበዓል ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ መሰል ድርጊቶች ራሳቸውን በምን መልኩ ለመጠበቅ እንደተዘጋጁ አስረድተዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ባምላክ ፍቃዱ እንዳለችው፤ በበዓሉ ወቅት በኤሌክትሪክ አጠቃቀም የተነሳ አደጋ እንዳይከሰቱ መጠንቀቅ ተገቢ ነው።

”በበዓል ወቅት ከከሰል በሚወጣ ጭስ አደጋ እንዳይደርስብን መጠንቀቅ አለብን” ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰብለወንጌል ደሳለኝ ናቸው።

ኅብረተሰቡ ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን በመጠኑ በመመገብ ጤናውን መጠበቅና ከተጨማሪ ወጪ ራሱን ማዳን አለበት ነው ያሉት ።

ነዋሪዎቹ አሽከርካሪዎች ከበዓሉ ጋር በሚፈጠር መጨናነቅና በመጠጥ ሳቢያ የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የ2012 ዓ.ም የዘመን መለመጫ በዓል አከባበር ላይ ሊደርሱ ከሚችሉ የእሳትና ሌሎች አደጋዎች ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክቱን አስተላልፏል።

በመልዕክቱ በመኖሪያ ቤትና ምግብ በሚያሰናዱ ተቋማት የጋዝና ኤሌክትሪክ ምድጃዎች አግባብ ባልሆነ መንገድ መጠቀም እንደማይገባ፣ የከሰል ምድጃ በቤት ውስጥ ስንጠቀምም በርና መስኮት በመክፈት በቂ የአየር ምልልስ ማድረግ ይገባል የሚል መልዕክትን አስተላልፏል።

በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ የተለያዩ መሳሪያዎች መሰኪያዎችን በአንድ ሶኬት ላይ ደራርቦ መጠቀም እንደማይገባና የኤሌክትሪክ እሳት ቢነሳ ከምንጩ ሳይቋረጥ በውሃ ማጥፋት መሞከር ተገቢ አለመሆኑንም ገልጿል።

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በሚኖር መዝናናት መጠጥ አብዝቶ ጠጥቶ ማሽከርከር ሊያደርስ የሚችለውን የህይወትና ንብረት ውድመት በማሰብ ጠጥቶ ከማሽከርከር መቆጠብ እንደሚገባም አሳስቧል።

ኅብረተሰቡ ማንኛውም የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም የአምቡላንስ አገልግሎት ለማግኘት 939 ነፃ የስልክ ጥሪና የማዕከሉን ስልክ ቁጥር 0111555300/0111568601 መጠቀም እንደሚችልም ተገልጿል።

አስተያየት ሰጪዎቹም አዲሱ አመት የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሁም ከዘረኝነት አስተሳሰብ ተላቀን ኢትዮያዊነትን ተላብሰን የምንኖርበት እንዲሆን ተመኝተዋል።

ምንጭ ፦ኢዜአ

You might also like
Comments
Loading...