Fana: At a Speed of Life!

800 ኪሎ ሜትሮችን ወደኋላ በመራመድ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ለመገናኘት ያለመው ኢንዶኔዢያዊ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 1 ፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢንዶኔዢያዊው ግለሰብ ለአካባቢ ጥበቃ ሲል እያደረገ ያለው ተግባር የበርካቶችን ቀልብ መሳብ መቻሉ ተነግሯል።

የ43 ዓመት ጎልማሳ የሆነው ኢንዶኔዢያዊው ሜዲ ባስቶኒ 800 ኪሎ ሜትሮችን ወደኋላ እየተራመደ ለመጨረስ ጉዞ መጀመሩ ነው የተነገረው።

ግለሰቡ ከመኖሪያ መንገደሩ ምስራቅ ጃቫ እስከ ኢንዶኔዢያዋ ዋና ከተማ ጃካርታ ድረስ ወደኋላ እየተራመደ የሚጓዝ ሲሆን፥ የጉዞው መጨረሻ ላይም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ለመገናኘት አልሟል ነው የተባለው።

ሜዲ ባስቶኒ በምስራቅ ጃቫ ከምትኘው ዶኖ ገጠራማ አካባቢ የተነሳው  ሀምሌ 18 ሲሆን፥ የኢንዶኔዢያ የነጻነት በዓል በሚከበርበት ነሃሴ 11 ጉዞውን በማጠናቀቅ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጋር ለመገናኘት ማቀዱም ተሰምቷል።

የጉዞው ዋነኛ ዓላማም የኢንዶኔዢያው ፕሬዚዳንት በመኖሪያ መንደሩ አካባቢ በሚገኘው ዊልስ ተራራ ላይ ችግኝ እንዲያስተክሉ ለመጠየቅ እንደሆነ ተሰምቷል።

ከዚህ ቀደም በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪ አክቲቪስቶች በርካታ ነገር ተናግረዋል ያለው ሜዲ ባስቶኒ፥ ይህንን ለማድረግ ያነሳሳው ደግሞ ችግሩ እየከፋ መምጣቱን ከንግግር እና ከጽሁፍ በተጨማሪ በአካል ለማሳወቅ ነው ብሏል።

ወደኋላ እየተራመደ 800 ኪሎ ሜትሩን ለመጓዝ ያሰበውም ባለፉት ጊዜያት ለኢንዶኔዢያ መልካም ተግባርን የፈፀሙ ጀግኖችን ወደኋላ ተመልሶ ለማሰብ እንደሆነም አስታውቋል።

ምንጭ፦ www.odditycentral.com

You might also like
Comments
Loading...