Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ ህንድ ቢዝነስ ፎረም ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 7 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያና የህንድ ኩባንያዎች የፊት ለፊት ምክክር መድረክ የሆነው የኢትዮ-ህንድ ቢዝነስ ፎረም ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብና የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስርን ማጠናከር አላማው ባደረገው የቢዝነስ ፎረም ከኢትዮጵያ እና ህንድ የተውጣጡ 40 ኩባንያች ተሳትፈውበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ደዋኖ ከድር፥ ኢትዮጵያና ህንድ የረጅም ጊዜ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መሰል መድረኮች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው ያሉት አምባሳደሩ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው ጀምሮ የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታት እየተሰሩና በሂደት ላይ ባሉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የህንድ አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዋና ጸሀፊ ሱናንዳ ራጀንድራን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እያደረገች ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አንስተው፥ የህንድ ኩባንያዎች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በምግብና ወተት ማቀነባበር እና በኢንፎርሜሽን ዙሪያ መሰማራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

በፎረሙ ላይ ከተሳታፊ ኩባንያዎቹ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የውሀ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተወካዮች ተካፍለውበታል።

የፎረሙ ተሳታፊ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ቆይታዎች በተመረጡ የኢንቨስትመንት ስፍራዎች ጉብኝት እንደሚያደርጉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like
Comments
Loading...