Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ በቀጣይ ዓመት ክልሉን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዷል

አዲስ አበባ፣ነሃሴ 6፣ 2011(ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ በቀጣይ ዓመት በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ  የቱሪስት መስህቦችን ከሚጎበኙ ቱሪስቶች ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት አቅዷል።

የቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተሩ አቶ መልካሙ አዳም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት ይህን ገቢ ለማግኘት ከ 16 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ፤ ወደ 5 መቶ ሺ የሚጠጉ ደግሞ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች እንዲጎበኙ እቅድ ተይዟል።

ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከውጭ ሀገር እና ከሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

ከተገኘው ገቢ ውስጥ ወደ አንድ ቢሊየን ብር የሚሆነው ክልሉን ከጎበኙ ከ 270 ሺ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው ደግሞ 11 ሚሊየን በላይ ከሚሆኑ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች  የተገኘ  መሆኑን ገልጸዋል።

የቱሪስት ፍሰቱ እና የተገኘው ገቢ ከታቀደው አንፃር ሲታይ ከ 70 እስከ 80 በመቶ አፈፃፀም ያለው መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፥ ለእቅዱ ሙሉ በሙሉ አለመሳካት ደግሞ በክልሉ ተፈጥረው የነበሩት አለመረጋጋቶች ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

በዙፋን ካሳሁን

You might also like
Comments
Loading...