Fana: At a Speed of Life!

የብሄራዊ ኩራት ቀን የፊታችን ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 17፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ብሄራዊ ኩራት ቀን የፊታችን ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ.ም በመዲናዋ እንደሚከበር አስታወቀ፡፡

ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓመት ምህረት በሚካሄደው የብሄራዊ የኩራት ቀን ዙሪያ የከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ ዛሬ ማምሻውን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመደመር እሳቤ የሰነቁ መርሃ ግብሮች ከጳጉሜን 1 እስከ ጳጉሜን 6 ባሉ ቀኖች መሰየማቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም ጳጉሜም 3 ቀን የብሄራዊ የኩራት ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡

የብሄራዊ የኩራት ቀን ብሄራዊ እሴቶቻችንን አጉልተን የምናሳይበት እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እንዲተባበር መነቃቃትን መፍጠር በሚያስችል መልኩ በመዲናዋ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ነው ወይዘሪት ፌቨን የገለጹት፡፡

ከ250 ሺህ በላይ ሰው ተሳታፊ የሚሆንበት ህዝባዊ ትዕይንት በመስቀል አደባባይ በዚሁ ዕለት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድም ነው የፕሬስ ሴክሬታሪዋ የተናገሩት፡፡

ብሄራዊ ኩራት የሆኑ እሴቶቻችን እና ሃገራዊ ተቋሞችን የሚገልፁ ክንውኖች መዘጋጀታቸውንም አንስተዋል፡፡

በዕለቱ የመከላከያ ሰራዊት እና የአየር ሃይል ትርዒት ያቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች እና የበረራ ሰራተኞችን ጨምሮ ብሄራዊ ኩራት የሆኑ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ተቋማት የሚወከሉበት ትርዒት መዘጋጀቱንም ነው የተናገሩት፡፡

የቡና ስርዓትን ጨምሮ ኢትዮጵያዊ እሴቶችን የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች እና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡበት መርሃ ግብርም ይኖራል፡፡

ከሰዓት በኋላ ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት መድረክ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡

በመጨረሻም ምሽት ላይ ለሃገር ባለውለታዎች እውቅና የሚሰጥበት እና የሃይማኖት መሪዎች በጋራ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የሚያስተላልፉበት ዝግጅትም ይኖራል ነው ያሉት፡፡

በዕለቱ በሚከናወኑ ልዩ ልዩ መርሃ-ግብሮች ላይ ነዋሪዎች በመሳተፍ የኩራታችን ምንጭ የሆኑ እሴቶቻችንን በጋራ እናወድስ ሲሉም በከተማ አስተዳደ ሩስም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብሄራዊ የኩራት ቀን “አዲስ አበባ ቤቴ፤ ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ!” በሚል መሪ ቃል የፊታችን ጳጉሜን 3 በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ እንደሚካሄድ ከከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like
Comments
Loading...