Fana: At a Speed of Life!

የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል በክልል ደረጃ በባህርዳር እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ፣ነሃሴ 19፣2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የሻደይ፣አሸንድዬና ሶለል በዓል በክልል ደረጃ ለ2ኛ ጊዜ በባህርዳር ከተማ እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳውን ጨምሮ የተለያዩ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ታድመዋል።

በዓሉ በአማራ ክልል ዋግኸምራ ሻደይ፣ በላስታ ላልይበላ አሸንድዬ፣ በራያ ቆቦ አካባቢ ሶለል በሚል መጠሪያ ሲከበር መሰንበቱ ይታወሳል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ በአማራ በክልል ደረጃ በባህር ዳር ከተማ እየተከበረ ሲሆን፥ የልጃገረዶች ጭፈራን ጨምሮ በርካታ ደማቅ በህላዊ ትዕይንቶች በጎዳና ላይ እየቀረቡ ይገኛሉ።

በዓሉ “የሻደይ፣አሸንድዬ እና ሶለል በዓል የአንድነታችን መገለጫ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተከበረ የሚገኘው።

በተመሳሳይ የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓል ከክልል ባለፈ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ሲከበር መቆዩቱ ይታወቃል።

በዛሬው ዕለትም የበዓሉ የመጨረሻ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ በሚሊኒዬም አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ የሚከበር መሆኑ ታውቋል።

የሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል በዓል ክዋኔ ሕጻናትን፣ ወጣቶችን እና እናቶችን ያለ ልዩነት የሚያሳትፍ ደማቅ፣ ውብና ሁሉን አቀፍ ባሕል ሲሆን፥በተለይ ወጣት ልጃገረዶች በጉጉት፣ በናፍቆት፣ በፍቅርና በልዩ ዝግጅት የሚጠብቁት በዓል ነው።

You might also like
Comments
Loading...