Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 100 ከፍተኛ መኮንኖች አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 4፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመከላከያ አዛዥነት ስታፍ ኮሌጅ ለ13ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 100 ከፍተኛ መኮንኖች አስመረቀ።

ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተከናወነ ስነ ስርዓት የተመረቁት 100 ከፍተኛ መኮንኖች ውስጥ 92 ፖስት ስታፍ እና ስምንት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥም 21 ተመራቂዎች ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ መሆናቸው በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል።

እነዚህ ተመራቂዎችም ከጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን የተውጣጡ መሆናቸው ነው የተመለከተው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድም ለተመራቂዎች ዲፕሎማ ከሰጡ በኋላ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ተመራቂዎች በስነ ምግባር፣ በወታደራዊ ጥበብ፣ በሙያዊ ብቃት እና በላቀ ዝግጅት የሰራዊት አባላትን ለመምራት እና ለድል ለማብቃት የሚያስችላቸውን እውቀት እና ከህሎት ለማግኘት ለአንድ ዓመት ትምህርታቸውን መከታተላቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም በትምህርት የገበዩትን እውቀት ከዚህ በፊት ካገኙት ልምድ፣ በንባብ ከሚያገኙት እና በተፈጥሮ ከያዙት እውቀት ጋር በማዋሃድ በትጋት ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

ወታደራዊ ተቋማት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ መሪዎች፣ በስነ ምግባር አርዓያዎች፣ ሀገርን እና ወገንን በመጠበቅ አኩሪዎች፣ ህግና ስርዓትን በማክበር እና በማስከበር ተምሳሌት እንዲሆኑም ያስፈልጋል ብለዋል።

 

በኃይለየሱስ ስዩም

 

You might also like
Comments
Loading...