Fana: At a Speed of Life!

ወደ ሃገር ቤት ሙሉ በሙሉ ስለመመለሳችን መረጃ ብናቀርብም በ40/ 60 የቤት መርሃ ግብር ተጠቃሚ አልሆነም- ከተለያዩ ሀገራት የተመለሱ ዜጎች

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 15፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከተለያዮ አረብ ሃገራት እና ከጎረቤት ሃገራት የተመለሱ ዜጎች ወደ ሃገር ቤት ሙሉ በሙሉ ስለመመለሳችን መረጃ ብናቀርብም በ40/ 60 የቤት መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንድንሆን አልተደረገም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሚኖሩበት ሃገር ኤምበሲ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ሃገር ቤት ሙሉ በሙሉ ስለመመለሳቸው የሚያስረዱላቸውን ማስረጃዎች መያዛቸውን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊንን በ40/60 የቤት ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ፣ በ2005 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የምዝገባ መርሃ ግብር መዘጋጀቱ ይታወሳል፡፡

በተለያዮ ሃገራት የሚኖሩ ዜጎች በውጭ ምንዛሬ ወይም በዶላር ባንኩ ባስቀመጣቸው መስፈርቶች መሰረት ሲቆጥቡ ቆይተዋል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር የሚጠቀሙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሃገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ መመለሳቸው ሲረጋገጥ ቁጠባቸዉ ከውጭ ምንዛሬ ወደ ብር የሚቀየርላቸው የቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በ2009 ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ መሰረት ማረጋገጫ ሲያቀርቡ ነው።

ወደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅሬታቸዉን ይዘው የቀረቡ እና በውጭ ሃገር ይኖሩ የነበሩ ዜጎች፣ ምንም እንኳን ስንኖርበት ከነበረው ሃገር ኤምባሲ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሙሉ በሙሉ ወደ ሃገር ቤት መመለሳችንን የሚገልጽ ማረጋገጫ ብናቀርብም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሊያስተናግደን አልቻለም ይላሉ፡፡

የቤት እድል ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው መርሃ ግብሩ እንደማንኛውም ሃገር ውስጥ እንደሚኖር ዜጋ ሊመቻች እንደሚገባም ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚያነሱት።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ለመሆኑ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለሚያነሱት ሀሳብ ምን ምላሽ አለው ሲል ጥያቄ አቅርቧል።

የኤጄንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ወደ ሃገር ቤት የተመለሱ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሁለተኛዉ ዙር የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ ፣ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሃገር ስለመመለሳቸዉ በማረጋገጥ ማስረጃዎችን የመስጠት ስራዎች በኤጄንሲዉ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል ወጥነት ያለው አሰራር ባለመኖሩ በጉዳዮ ዙሪያ ቅሬታዎች አሁንም ድረስ እንደሚነሱ ዋና ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል ፡፡

ኤጄንሲው አሁንም አስፈላጊዉን ማስረጃ በመመልከት ለዜጎች ተገቢ ምላሽ የመስጠቱ ስራ እንዳላቆመም ወይዘሮ ስላማዊት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ የተመለሱት ዜጎች በመኖሪያ ቤት ልማት እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚስተናገዱበት መመሪያ ከዚህ ቀደም አለመኖሩ ለችግሩ መከሰት ምክንያት ሆኗል ብሏል፡፡

የባንኩ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ያብስራ ከበደ የኢትዮጰያ ንግድ ባንክ አሁን ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው አዲሱ መመሪያ የመኖሪያ ቤት እጣ የወጣላቸዉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ወደ ሃገር ቤት የገቡ ዜጎችን ቅሬታ የሚፈታ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

መመሪያው ቅሬታቸውን ላቀረቡ ዜጎች የሚያነሱትን የብድር አቅርቦት ጥያቄ የሚፈታ ይሆናል፡፡

መመሪያው ይህን ስራ እያስተባበሩ ለሚገኙ ባለድርሻዎች መተላለፉም ተገልጿል፡፡

አወል አበራ

You might also like
Comments
Loading...