Fana: At a Speed of Life!

ከህብረተሰቡና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በተሰራው ስራ የክልሉን ሰላም ማስጠበቅ ተችሏል- አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 7፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከህብረተሰቡ እና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በጋራ በተሰራው ስራ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ መቻሉን የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።

ርእስ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ በነበሩ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት በተሰሩ ስራዎችና በተገኙ ውጤቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ተመስገን በማብራሪያቸውም፥ በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ችግር የክልሉ ርእሰ መስተዳድርን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችን እንዲሁም በፌደራል ደረጃም የጦር ሀይሎች ከፍተኛ ጄነራሎች መሰዋት መሆናቸው ይታወሳል ብለዋል።

ይህንን ተከትሎም የክልሉ ህዝብ እና የፀጥታ አካላት ከፌደራል የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በሰሩት ስራ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር እንዳይሰፋ እንዲሁም ጉዳቱን ያደረሱ ሰዎች በቁጠጥር ሰር እንዲውሉ ፈጣን የሆነ ስራ በመስራታቸው ችግሩ ሳይፋፋ መቅረቱን አስታውቀዋል።

አሁን በክልሉ ለመጣው ሰላምም መላው የክልሉ ህዝብ እና ሌሎች ክልሎች ከጎናቸው በመሆናቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉንም ነው አቶ ተመስገን የገለጹት።

የበርካታ ክልሎች ርእሳነ መስተዳድሮችም በባህር ዳር በተካሄደው ባዕለ ሲመታቸው ላይ ተገኝተው ያሰሙት የአጋርነት መልእክትም የበለጠ እንዲሰሩ እንዳገዛቸውም ተናግረዋል።

የፀጥታ ሀይሉም የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ በመተማመን እና እስከ ታችኛው አባላቱ ድረስ በመወያየት እንዲሁም ሁሉንም የሀብረተሰብ ክፍል በማወያየት ሌሎች ችግሮች እንዳይፈጠሩ ተባባሪ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ በመሰራቱ መረጋጋቱ ታይቷል ብለዋል።

ባሳለፍነው እሁድ የተከበረው የአረፋ በዓል በክልሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር መጠናቀቁ እና ባህር ዳር ላይ ፋሲል ከነማ ያደረገው ዓለም አቀፍ ጨዋታም ያለምንም ችግር መጠናቀቁ የክልሉን ገጽታ የቀየረና ሰላም መኖሩን ያረጋገጠ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

ለዚህም የክልሉን ህዝብ በተለይም የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎችን፣ የፋሲል ከነማ አመራሮች እና ደጋፊዎችን እንዲሁም ለፀጥታ ሀይሉ ምስጋና አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ በሁሉም አቅጣጫ ሰላማዊ ሁኔታ ነው ያለው ያሉት አቶ ተመስገን፥ አሁን የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በቀጣይም በክልሉ የፀጥታ ችግር ካለ በህብረተሰቡ ጋር በመሆን በመከላከል በቀጣይ ክልሉን ወደ ልማት ስራ ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሰራም ነው የገለጹት።

አቶ ተመስገን አክለውም፥ በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እና ሰላምን ለማምጣት ሁሉም አካል በጋራ መስራት እንዳለበትም መልእክት አስተላልፈዋል።

የህግ የበላይነትን የሚጥሱ አካላት ላይም ያለርህራሄ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም ነው ርእሰ መስተዳድሩ ያስታወቁት።

ሰላም ሲሆን ሁሉም ጥያቄዎች መፍትሄ ማግኘት ይችላሉ ያሉት አቶ ተመስገን፥ የመሰረተ ልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት እና መሰል ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት ስላም ሲኖር በመሆኑ ሁሉም ለሰላሙ ዘብ መቆም እንዳለበትም ጥሪ አቅርበዋል።

ከሰላም በተጨማሪ የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎችን ለመገምገም ድንገተኛ ጉብኝት ማድረጋቸውን ገልፀው፥ በጉብኝታቸውም ክፍተቶች እንዳሉ መለየቱን ገልፀዋል።

መሰል ጉብኝቶችን በተከታታይነት በማድረግ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አንደሚሰራም አስታውቀዋል።

እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራው ላይም በቀጣይ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶበት የሚሰራ ጉዳይ መሆኑንም አክለው ገልፀዋል።

በቀጣይም የአማራ ክልል ሰላም እንዲሆን እና ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች መጥተው የሚሰሩበት ክልል ለማድረግ በትኩረት ይሰራልክ ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉ ህዝብም ለሰላሙ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

 

You might also like
Comments
Loading...