Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳና የብሪታኒያ የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 16፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የብሪታኒያ የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞንን ጎብኝተዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳና የብሪታኒያ የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ በኢንዱስትሪ ዞኑ ባደረጉት ጉብኝትም የዩኒሊቨር ኩባንያ ስራዎችን ተዘዋውረው መመልከታቸውን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት፥ አርሶ አደሩን፣ ወጣቶችን እና ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢንቨስትመንቶችን ወደ ክልሉ ማምጣትና ድጋፍ ማድረግ ግዴታችን ነው ብለዋል።

ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት።

የብሪታኒያ የዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር አሎክ ሻርማ በበኩላቸው፥ መንግስታቸው በኢትዮጵያ ለሚደረጉ ኢንቨስትመንት ስራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳና አሎክ ሻርማ ከጉብኝቱ በኋላም በዱከም ከተማ በጋራ በመሆን የችግኝ ተከላ ያካሄዱ ሲሆን፥ የዱከም ከተማ ነዋሪዎችም የተለያዩ ስጦታዎችን አበርክተውላቸዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋም የሆነው ዩኒሊቨር ኩባንያ በዱከም በሚገኘው ኢስተርን ኢንደስትሪ ዞን ውስጥ ለምግብነት እና ለመዋብያነት የሚያገለግሎ ምርቶችን እያመረተ ለገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል።

ኩባንያው በኢንደስትሪ ዞኑ ባለው ፋብሪካም ከዚህ ቀደም ክኖር የምግብ ማጣፈጫ፣ ላይፍ ቦይ የንፅህና መጠበቂያ ሳሙና እና ቫዝሊን ሎሽን እያመረተ ይገኛል።

ባሳለፍነው መጋቢት ወርም የሲግናል የጥርስ ሳሙና ማምረቻ ፋብሪካውን በይፋ ስራ ማስጀመሩም ይታወሳል።

You might also like
Comments
Loading...